Article

Article

ተዋጊ

Home Blog Book About Contact X Order Book ተዋጊ Audio ሰሞኑን እየተማርኩ ያለሁት ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ነው። “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም ደግሞ እግዚአብሔር ነው” በማለት በዘጸአት 15፡3 ላይ እንደተጻፈው፥ የምናመልከው አምላክ ተዋጊ እንደሆነ ሁሉ እኛም ህዝቦቹ ተዋጊ ሰራዊቶች እንድንሆን ይፈልጋል። አንድ ጊዜ እንዲያውም በመሳፍንት መጽሐፍ ምእራፍ 3 ከቁጥር 1 ጀምሮ ስትመለከቱ፥ እግዚአብሔር ሆነ ብሎ የእስራኤል ልጆች መዋጋትን ይማሩ ዘንድ፥ ሰልፍን ይለማመዱ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ጠላቶቻቸውን ሊያጠፋ እንዳልወደደና ጥቂት ጠላቶችን እንዳስቀረ በክፍሉ ላይ ይናገራል። እግዚአብሔር መዋጋትን እንድናውቅ፥ ሰልፍን እንድንማር ይፈልጋል። ዳዊትም በመዝሙረ ዳዊት 144 ላይ ስለ ጎልያድ በጻፈው መዝሙር ላይ “እግዚአብሔር አምላኬ ይባረክ፥ ለእጆቼ ሰልፍን ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር” በማለት እግዚአብሔር መዋጋትን ያስተምረው እንደነበር ተናግሯል። ዳዊት እንዲያውም ጎልያድ ጋር ሲመጣ አይደለም ውጊያን የተማረው። በምድረበዳ የአባቶቹን በጎች ሲጠብቅ፥ እግዚአብሔር አንበሳና ድብን እየላከ ነው ውጊያን አስቀድሞ ያለማመደው። እንዲያውም ጎልያድን ለመግጠም ወደ ሳኦል ማመልከቻ ሲያስገባ፥ እንደ ልምድ አድርጎ ያቀረበው ምድረበዳ ላይ በአንበሶችና በድቦች ላይ እግዚአብሔር የሰጠውን ድሎቹን ነበር። “ሳኦልም ዳዊትን። አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው። እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ዳዊትም። ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ።” (1ኛ ሳሙኤል ምእራፍ 17፡33-37)  ዳዊት ምድረበዳ ላይ በጎች እየጠበቀ ለእግዚአብሔር ይዘምራል። አንበሳና ድብ ደግሞ በጎን በኩል ይመጡበታል። አንድም ቀን ግን “እግዚአብሔር ሆይ እኔ ለአንተ እየዘመርኩ፥ እኔ አንተን እያመለኩ፥ እኔ ለአንተ እየኖርኩ እንዴት ህይወቴን አደጋ ላይ የሚጥሉ አራዊቶች ሲመጡብኝ ዝም ብለህ ትመለከታለህ?” ብሎ ሲያጉረመርም አንሰማውም። ይልቁንም “እግዚአብሔር ብርሀኔና መድሀኒቴ ነው የሚያስፈራኝ ማነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው የሚያስደነግጠኝ ማነው?” እያለ በእግዚአብሔር ላይ በመታመን ይዘምራል። መታገል ሲያቅተው ደግሞ ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እየጠራ ከጠላቶቹ እጅ ይድናል።   አንድ ሰው አለምን ሰይጣንንና የራሱን ፈቃድ ትቶ ክርስቶስን ለመከተል ሲወስን፥ ወዲያውኑ የሰይጣን መንግስት ጠላት ይሆናል። ስለዚህ ሁልጊዜ ጠላት አለን፥ ሁልጊዜ ውጊያ ውስጥ ነን ማለት ነው። ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ስናስብ ውጊያውን ብዙ ጊዜ የምናያይዘው በተለያዩ አጋጣሚዎች መንገዳችን ላይ ከሚመጡ አደጋዎች፣ የጤና መቃወሶች እንዲሁም አለመከናወኖች ጋር ብቻ ነው። ጠላት በእነዚህ መንገዶች ሊዋጋን ቢችልም በየቀኑ እኛን የሚዋጋበትን ዋና መንገድ ግን ቸል ልንለው አይገባም። በኤፌሶን መጽሐፍ ምእራፍ 6 ከቁጥር 10 ጀምሮ እንደተጻፈልን ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር እንድንታጠቅ የተነገረን፥ የዲያቢሎስን ሽንገላ እንድንቃወም ነው። ወገባችንን በእውነት እንድንታጠቅ፣ የጽድቅን ጥሩር እንድንለብስ፣ በሰላም ወንጌል እግሮቻችን ተጫምተው እንዲቆሙ፣ የመንፈስን ሰይፍ እንድንይዝ የተነገረን፥ የዲያቢሎስን ሽንገላ እና ውሸት እንቃወም ዘንድ ነው።  በየቀኑ ሰይጣን ወደ አይምⶂአችን የሚልከውን ውሸቶች የምንቃወምበት ዋና መሳሪያችን ደግሞ፥ እውነት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው። ውሸት የሚጋለጠው በእውነት ነው። ውሸት ውሸት መሆኑ የሚታወቀው እውነት ሲመጣ ነው። እውነት ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ስለዚህ ጠላት ወደ ሀሳባችን የሚልካቸውን ውሸቶች መቃወም የምንችለው፥ በተጻፈልን የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው ማለት ነው። እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችሃል በማለት በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 8፡32 ላይ እንደሚናገረው፥ የምናውቀው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው አርነት የሚያወጣን።   ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን ጌታና አዳኝ አድርገን በተቀበልንበት በዚያች ደቂቃ፥ አዲስ ፍጥረት ሆነናል፥ አዲስ ማንነት ተሰቶናል። ነፍሳችን የዳነችው፥ የክርስቶስን ስራ በእምነት በተቀበልንበት በዚያች ቅጽበት ነው። አያችሁ ግን እምነት እንዴት አስፈላጊ እንደሆነ? “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና” ተብሎ በኤፌሶን 2፡8 ላይ እንደተጻፈው፥ የእግዚአብሔር ጸጋ ያዳነን እግዚአብሔር እራሱ በሰጠን እምነት ውስጥ አልፎ ነው። ምንም ኢየሱስ ለሀጢያታችን ዋጋ ቢከፍልም፥ ይሄንን እውነት በእምነት ካልተቀበልነው ልንድን አንችልም። እምነት ዘላለማችንን ከገሀነም አስመልጦ ወደ እግዚአብሔር መንግስተ እንገባ ዘንድ እግዚአብሔር የተጠቀመበት አስደናቂ ነገር ነው። ዘላለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ማዳን የሚያልፈው በእምነታችን ውስጥ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት የጀመርነውን ይሄንን መንገድ እስከመጨረሻው የምንቀጥለውም በእምነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ የተሰጠንን ነጻነቶች አስጠብቀን የምንኖረው በዚሁ እግዚአብሔር በሰጠን እምነት ውስጥ ነው።  እግዚአብሔር እንዲሁ በነጻ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ የሰጠን፣ እንደተሰጠን ባለማወቃችን ግን እንዳልተሰጠው ሰው የምንኖርባቸው ብዙ ሁኔታዎች አሉ። በሀገራችን አንድ አባባል አለ “የሌለውና ያለውን የማያውቅ አንድ ናቸው” ሲባል ሰምቻለው። ምንም በጠላት ሀይል ሁሉ ላይ ስልጣን ቢሰጠንም፥ የተሰጠንን ነገሮች ካላወቅን ስለማንጠቀምበት መብት ከሌለው ሰው ጋር ልዩነት ላይኖረን ይችላል።   ስለዚህ ጠላት እኛን በባርነት ውስጥ ለማስቀመጥ እድል የሚያገኘው በሁለት መንገዶች ብቻ ነው። ወይ ስለ እኛ የተጻፈውን ቃል ባለማወቃችን ነው ወይንም ደግሞ ያወቅነውን ቃል ባለማመናችን ውስጥ ነው። ስለዚህ የሚያደርገው ከሁለቱ አንዱን ነው፥ ወይ እንዳናውቅ ይታገላል። ወይንም ደግሞ ያወቅነውን እንዳናምነው ይታገላል። ምክኒያቱም ፍጹም የሆነው ነጻነታችን ያለው እውነትን በማወቃችን እና ያወቅነውን እውነት በማመናችን ውስጥ ነው። በ1ኛ ዮሐንስ 5፡4 ላይ ሲናገር፥  “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ አለምን ያሸንፋልና፥ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው” በማለት እንደተናገረው እምነት በክርስቶስ የተሰጠንን አሸናፊነት ጠብቀን የምንኖርበት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። እምነት መንፈሳዊ አለም ላይ እጅግ የከበረ ነገር ነው። የጠላት ውሸት ዘልቆ ወደ ውስጣችን እንዳይገባ የምንከላከልበት ጋሻችን ነው። ብርቱ የሆነ የመዋጊያ መሳሪያችን ነው። እግዚአብሔርም በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሕይወታችንን የሚያሳልፍበት ምክኒያት፥ በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነው እምነታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ ነው። ሰይጣን የፈለገ ሀይለኛ ቢሆን እንካን ከተጻፈው ሕግ አልፎ ሊሰራ አይችልም። ሊሰራ የሚችለው ህጉን ባለማወቃችን ምክኒያት የሚያቀርብልንን ውሸቶች በማመናችን ውስጥ ብቻ ነው።  ፍርድ ቤት ከሳሽና ተከሳሽ በዳኛው ፊት በቆሙበት የፍርድ ወንበር ፊት ዳኛው የከሳሽንና የተከሳሽን ሀሳብ ካዳመጠ በሓላ ፍርዱን ከመስጠቱ በፊት አንድ ወሳኝ የሆነ ጥያቄ ይጠይቃል። “ህጉ ምን ይላል” ይላል። በጉዳዩ ላይ ቀድሞ የተጻፈው ህግ ምን ይላል? አያችሁ ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ ወደ ፍርድ ቤቱ ሳይመጡ በፊት በሚካሰሱበት ጉዳይ ዙሪያ አስቀድሞ የተጻፈ ህግ አለ። ሊፈርድ የተቀመጠው ዳኛ ፍርዱን የሚሰጠው አስቀድሞ በተጻፈው ህግ መሰረት ነው። ህጉ መተዳደሪያ፣ ትክክለኛ ፍርድ መፍረጃ ነው። ጠበቆችም ለመከራከርና የከሳሹን ወይንም የተከሳሹን መብት ለማስከበር ያላቸው ብቸኛ መንገድ ሕጉ ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል ብለው የተጻፈውን ህግ በመጥቀስ መብታቸውን ለማስከበር መትጋት ነው። መንፈሳዊ አለም ላይ የሚሰራው የእግዚአብሔር ቃል ህግ ነው። ሰይጣንም ህጉን ያውቃል፥ በደምብ ከእኛ የበለጠ ያውቃል። ትዝ አይላችሁም ኢየሱስን ቃል እየጠቀሰ ሊፈትነው ሲሞክር? ለዚያ ነው የእምነትን ጋሻ ማንሳት ያለብን፣ የመንፈስ ሰይፍ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ማንሳት ያለብን። የምንዋጋበትና ነጻ የምንወጣበት ትልቁ መሳሪያችን አምነን የምንዋጋበት የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ነው።  የብሉይ ኪዳን መጽሀፍን ስናነብ በኢያሱ መጽሐፍ ላይ ኢያሱና ሕዝቡ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን  ለመግባት መንገዳቸው ላይ ያሉትን የእግዚአብሔር ጠላት የሆኑትን ሕዝብ በመዋጋት እና ምድሪቱን በመውረስ የተስፋ ቃላቸው ጋር መድረስ ነበረባቸው። እግዚአብሔር አስቀድሞ “የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ለእናንተ ሰጥቻለሁ” በማለት ምድሪቱን እንደሰጣቸው አስቀድሞ ስለተናገረ፣ እነ ኢያሱ እግዚአብሔር ሰጥቻችሁዋለሁ ብሎ በሰጣቸው ምድር ላይ ከተቀመጡት ጠላቶች ጋር ሲዋጉ እምነታቸው ይሄ ነበር “ምድሪቱን እግዚአብሔር ሰጥቶናል፣ ምድሪቱ የእናንተ አይደለችም የእኛ ናት” የሚል ታላቅ እምነት ልባቸው ውስጥ ነበር። የእነ ኢያሱ መፈክር፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን ስለሰጠን እናስለቅቃችሃለን” የሚል ነበር። ምንም በጠላቶች ተይዛ የነበረች ምድር ብትሆንም፥ እነ ኢያሱ እነዚህን ጠላቶች ለማስለቀቅ፥ እግዚአብሔር “ለእናንተ ሰጥቼዋለሁ፣ የእናንተ ነው” ያለውን ቃል አምነው መዋጋት ነበረባቸው። እግዚአብሔር የሰጣቸውን

Article

ብልጫ

Home Blog Book About Contact X Order Book ብልጫ Audio ዛሬ አንድ ነገር አስብ ነበር። በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያሉ መንታ ወንድማማቾች ያእቆብና ኤሳው። በ27ተኛው ምእራፍ ላይ ነው ይስሐቅ ሸምግሎ አይኖቹ ለማየት በፈዘዙ ጊዜ፥ ታላቁን ልጁን ኤሳውን ጠርቶ “ልጄ ሆይ እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም። አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፤ ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።” በማለት ኤሳውን የሚጠይቀው። ኤሳው ታዲያ አባቱ ባለው መሰረት አደን ሊያድን ወደ ምድረበዳ ይሄዳል። ይሄን ጊዜ ነው እንግዲህ መረጃውን ከእናቱ በመስማት እና በእናቱ በመታገዝ ታናሽ ወንድሙ ያእቆብ በአቋራጭ ገብቶ የኤሳውን በረከት በሙሉ የወሰደው። በረከቱ እኮ ተስፋ የተገባው ለኤሳው ነበር። ይስሐቅ ሊባርክ የወደደውና በረከቱን በሙሉ መስጠት የፈለገው ለኤሳው ነበር። ያእቆብ ግን ፈጣን ነው፥ አባቱ የሚወደውን ነገር ይዞ ለመቅረብ ፈጣን ነው። የሚውለው እራሱ እዚያው አባቱ ያለበት ሰፈር፥ በረከት ያለበት አካባቢ ነው። እኔ ሳስበው እንደ ያእቆብ የበረከት ትርጉም የገባው ሰው ያለ አይመስለኝም። በኋላ ላይ እኮ ታሪኩን ስታነቡት፥ ስለ በረከት ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎ አሸነፈ የተባለለት አስገራሚ ሰው ነው። ያእቆብ ስለ በረከት ከወንድሙ ጋር ታግሏል፣ ከአጎቱ ከላባ ጋር ታግሏል፣ ከዚህም አልፎ ከእግዚአብሔርም ጋር ታግሏል። ከአብርሀም ጀምሮ እግዚአብሔር ሲገባላቸው የኖረው የተስፋ ቃል በደምብ እንደገባው አልጠራጠርም። የአብርሀም በረከትም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ እንዳለፈ ስለሚያውቅ ይመስለኛል በምስር ወጥና በእንጀራ አታሎ ከታላቅ ወንድሙ ከኤሳው ብኩርናውን የተቀበለው። አይገርምም? በረከት እኮ የታዘዘው ለታላቁ ነበር። ይስሀቅም የፈለገው ኤሳውን መባረክ ነበር። ያእቆብ ግን ፈጣን ነው፥ ውሎው ደግሞ እዚያው አባቱ ያለበት አካባቢ ነው። ውሎው የአባቱን ድምጽ ከሚሰማበት፣ የአባቱን ጠረን ከሚያሸትበት የራቀ አልነበረም። አባቱ የፈለገውን ነገር ለማወቅ እዚያው ቅርብ ነው፥ ብዙ አይርቅም። እዚያው የአባቱን ፍላጎት ቶሎ የሚሰማበት እና የሚያውቅበት ሰፈር ነው የሚውለው። እኛ ግን የት ነው የምንውለው? ውሎአችን የት ነው? የት ሰፈር ነው የምንውለው? መቼም ስለ geographical location አይደለም እያወራን ያለነው። ልባችን የት ሰፈር ነው የሚውለው? ጆሮአችን የት ነው ያለው? ቅርብ ነን? እዚያው እግዚአብሔር የሚገኝበት ሰፈር ነን ያለነው? ሲናገር ቶሎ የምንሰማበት፣ ፍላጎቱን የምናውቅበት ሰፈር ነን ያለነው? በረከት ያለበት ሰፈር ነው የምንውለው? ወይንስ እንደ ኤሳው ሩቅ ሰፈር ነው የምንውለው? እዚያው ድምጹ ሰፈር ነው ጆሮአችን ያለው? ወይንስ ሌላ ቦታ ነው ያለው? ምንድነው ቀኑን ሙሉ ስንሰማ የምንውለው? እንደ ኤሳው እኮ ብዙ የተስፋ ቃል ሊኖረን ይችላል። እግዚአብሔር እኮ ሊባርከን ፈልጎ ሊሆን ይችላል። እንደ ኤሳው እኮ አባቴ ይባርከኛል ብለን ተስፋ እያረግን ይሆናል ያለነው:: ዋናው ጥያቄ ግን የት ነው የምንውለው?  እዚያው ከተስፋ ሰጪው ሰፈር ነው የምንውለው? እግዚአብሔር ሲናገረን የምናዳምጥበት ቦታ ነው ያለነው? እግዚአብሔር ሲፈልገን የምንገኝበት ስፍራ ነው ያለነው?  በመዝሙር 89 ላይ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲናገር እንዲህ አለ። “ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት። እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች። ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም። ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ። እውነቴና ምሕረቴም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል። “አያችሁ እግዚአብሔር ምን አለ? ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት አለ። ዳዊት እግዚአብሔር ሲመጣ ያገኘው ሰው ነበር። ዳዊት ራሱን ለእግዚአብሔር ያስገኘ ሰው ነበር። ዳዊት ውሎው ልክ እንደ ያእቆብ እዚያው አባቱ ባለበት ሰፈር ነበር፥ ቅርብ ነበር። ውሎው በጎች እየጠበቀ ስራ ተሰጥቶት ምድረበዳ ላይ ሆኖ፥ ስራ ላይ ሆኖ እራሱ ዳዊት ዝማሬ ውስጥ ነው። አምልኮ ውስጥ ነው። የእግዚአብሔር ህግና ስርዓት ውስጥ ነው። ስራ ስለተሰጠው ቢዚ ነኝ፥ ስራ ላይ ነኝ ሳይል ልቡ እግዚአብሔርን ፍለጋ ላይ ነበር። ዳዊት በእግዚአብሔር የተቀባው እራሱን/ልቡን በእግዚአብሔር ሊገኝ የሚችልበት ስፍራ ላይ ስላስገኘ ነው። እግዚአብሔር ምን አለ? ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱሱንም ቅባት ቀባሁት አለ። የሆነ location አለ እግዚአብሔር እኛን ማግኘት የሚፈልግበት፣ ቅባቱ የሚፈስበት፣ የእግዚአብሔር ህልውና የሚፈስበት መንፈሳዊ ስፍራ አለ። ይሄ ቦታ አደባባይ ላይ አይደለም። ግርግር ውስጥ አይደለም። ሶሻል ሚዲያዎቻችን ውስጥም አይደለም። እግዚአብሔር እኛን ማግኘት የሚፈልግበት ልዩ የሆነ ቦታ አለ። የእኛ ስራ ቅባቱ ስር መቀመጥ ብቻ ነው። ቅዱስ ቅባቱ ከሚፈስበት ስር ራሳችንን ማስቀመጥ ብቻ ነው። ይሄንን ለማድረግ ታዲያ ውሳኔ እና ቆራጥነት ያስፈልጋል። መዝጋትም ካስፈለገ ብዙ መዝጋት ያለብን ሚዲያዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙ መተው ያለብን የማይጠቅሙን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እራሳችን እናውቃቸዋለን ሰው ይሄንን ይሄንን ማለት አያስፈልገንም። ይሄንን ማድረግ ከከበደን እና ጸጋ ካስፈልገን ደግሞ፥ እንጠይቀው እንጂ እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ የምንለምነውን ሁሉ የሚያደርግ እና በብዙ የሚረዳን መልካም አምላክ ነው። እኛ ፈቃዳችንን ሰጥተን እንለምነው እንጂ፥ ሀይል የእርሱ ነው፥ ማስቻል የእርሱ ነው፥ መንፈስ ቅዱስ እኮ የተሰጠን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ሕይወት እንኖር ዘንድ ድካማችንን ሊያግዝ ነው።  በረከቱ ለኤሳው ቢታዘዝም ያእቆብ በመገኘት በለጠ። በፍጥነት፣ የአባቱን ፍላጎት ለማድረግ ከእናቱ ጋር በመተባበር እና ቶሎ በማድረግ በልጦ ተገኘ። እራሱን በአባቱ ፍላጎት ውስጥ አስገኘ። አንዳንድ ጊዜ ወገኖቼ ብዙዎቻችን እግዚአብሔር ተስፋ ገብቶልኛል እንላለን። እውነት ነው እግዚአብሔር የተስፋ አምላክ ነው ብዙ ተስፋዎችንም ሰጥቶናል ነገር ግን ከእኛ የሚጠበቀውን እያደረግን ነው ወይ? ሌላው ቀርቶ እግዚአብሔር እንደተናገረው ሊባርከን ሲመጣ እና ልክ ይስሀቅ ልጁን ሊባርክ ፈልጎ አምጣልኝ ብሎ የሚፈልገውን እንደነገረው የበረከቱን መንገድ ሊያሳየን እና ሊናገረን ሲመጣ እኮ እኛ በቦታችን የለንም። ልባችን ሌላ ሌላ ቦታ ላይ ነው። ሀሳባችን በብዙ ሌሎች ጊዜያዊ እና ምንም ጥቅም በሌላቸው ተራ ነገሮች የተከፋፈለ ነው። የእግዚአብሔር ተስፋ እኮ የእኛን መገኘት፣ የእኛን መታዘዝ እና የእኛን ከእርሱ ጋር መራመድ የሚጠይቅ ነው። ብዙ እንጸልያለን ልንል እንችላለን፥ ግን ውሎአችን የት ነው? ወገኖቼ ጸልየን ጨርሰን ዝም ብለን በማይጠቅሙን ወሬዎች ውስጣችንን ስንሞላ ከዋልን፥ ጸሎታችን ብቻውን የትም አያደርሰንም። የተጠራነው የሕይወት ለውጥ እንድናደርግ ነው። ወደ ክርስቶስ እንድናድግ ነው፥ ወደፊት እንድንራመድ ነው። የተጠራነው እኮ ከእርሱ ጋር ለመኖር ነው።  መዝሙረኛው እኮ ቆይቼ የእግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት እንዳለው ይቻላል እኮ ሌላ ሌላውን ትቶ ከእግዚአብሔር ጋር መዋል ይቻላል። ቢዚ ሆነን እራሱ ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ይቻላል። እየነዳን ከእግዚአብሔር ጋር ማውራት ይቻላል፣ cook እያረግን ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ይቻላል፣ ስራ ቦታችን ሆነን እየሰራን ልባችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ይቻላል። እግዚአብሔርን ለማሰብና ለመፈለግ የሚከለክለን ምንም አይነት ህግም ቢዚነትም የለም። ምነው ምንስ ቢዚ ብንሆን ለሶሻል ሚዲያዎቻችን እና ለተለያዩ ምንም ለማይጠቅሙን ኢንፎርሜሽኖች ጊዜ አለን አይደል እንዴ? እንዲያውም የቢዚነታችን አንዱ ተባባሪ አካል ይሄ አይደለም እንዴ? ልባችንን የገዛው፣ ሀሳባችንን የማረከው፣ ፍቅራችንን የወሰደው የዘመኑ ጣኦት ይሄ አይደለም እንዴ? አሁን ላይ እኮ ኢንፎርሜሽን ሳንሰማ ከዋልን፣ ስለ ሰዎች ታሪክ ሚዲያ ላይ ሳንሰማ ከዋልን፥ የሆነ ነገር ከፍተን ሳንሰማ ከዋልን እኮ ምድር መሽከርከሯን የምታቆም ነው የሚመስለን። እስኪ እንጹም አሁን በዚህ ዘመን እኮ የምግብ ጾም ከሶሻም ሚዲያ እና ከሌሎች ነገሮች ጾም ይልቅ ቀላል ሆኗል።  ብዙ ኢንፎንሜሽን እያመለጠን ነው። ያምልጠና። በማይጠቅመን ዜናዎች መቅረት የቱ ጋር ነው ሕይወታችን የተጎዳው? መንፈሳዊ አለም ላይ የሚያመልጠንስ በረከት? አንዳንድ ጊዜ እኮ አበላልጠን የቱ እንደሚበልጥ አስበን መምረጥ የምንገደድባቸው እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች አሉ። አንዳንድ ጊዜማ ከነመፈጠራችን እኛን የማያውቁንን ሰዎች ታሪክና ፎቶግራፍ ስንከታተል እኮ ነው ክቡር ጊዜያችንን የምናጠፋው። ስንሰማ የምንውለው ነገር ሁሉ ምድራዊ ነገር ብቻ ሆኖ፥ ስጋዊ ክርስቲያኖች እያደረገን ነው። ስንሰማ ከምንውላቸው ነገሮች እየተወሰድን፥ ከአለማውያኖች ጋር በብዙ ነገር አንድ እየሆንን ነው። በሀሳብ፣ በንግግር፣ በድርጊት እየተመሳሰልን ነው። እስኪ አስቡት ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር የሚውል ሰው የመንፈስ ፍሬን ያፈራል። ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ በጎነትን፣ ቸርነትን፣ የዋህነትን፣ እግዚአብሔርን መፍራትን ያፈራል። ሌላ ሌላ ስጋዊ ነገር ሲሰማ የሚውል

Article

ሸክም

Home Blog Book About Contact X Order Book ሸክም Audio የነህምያን ታሪክ ሳጠና ከሕይወቱና ከአገልግሎቱ ከተማርኳቸው ጥቂት ነጥቦች ውስጥ፥ ምናልባት ለሰዎች የሚቀር ነገር ካለ ብዬ ለመጻፍና ለማካፈል ብእሬን አንስቻለሁ። ታሪኩን አብዛኞቻችን እንደምናውቀው፥ ነህምያ እግዚአብሔር በዘመኑ የነበረውን ሀሳብ ያገለገለበት አስገራሚ የእግዚአብሔር ሰው ነበር። በስራው የንጉስ ጠጅ አሳላፊ ሲሆን፥ ምንም አይነት የኑሮና የኢኮኖሚ ችግር ሳይኖርበት የሚኖር ሰው ነበር። እስራኤል በባቢሎን ምርኮ ተገዝታ ወደ ባቢሎን ስትማረክ፥ እርሱ ወይንም ቤተሰቦቹ ተማርከው ወደ ባቢሎን ከፈለሱት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ ከነህምያ ወንድሞች አንዱ የሆነውን አናኒን እንዲሁም ከአናኒ ጋር ከይሁዳ የመጡትን ሰዎች ነህምያ ይጠይቃል ። “ወንድሞቼ የመጣችሁት ከይሁዳ ነው። እስኪ ጥቂት ነገር ንገሩኝ፥ ይሁዳ እንዴት ናት? ከምርኮ የተረፉትስ የአይሁድ ሰዎች እንዴት ናቸው?” በማለት ወንድሞቹን ይጠይቃል። ነህምያ ይሄንን ጥያቄ የጠየቀው እንዲያው ለማወቅ ብቻ አልነበረም። የእግዚአብሔር ከተማ ስለሆነችው ስለ ኢየሩሳሌም በእርግጥም ግድ ስለሚለው ነው። አንዳንዴ እኮ እንዴት ነህ ወይንም እንዴት ነሽ ማለት ልማድ ስለሆነብን ሰዎችን እንጠይቃለን እንጂ የጠየቅነው ሰው ምንም ቢሆን ከልባችን ግድ ላይለን ይችላል። በተለይ ደግሞ ያንን ሰው ብዙም የማንቀርበው ከሆነ። ሰላም ነው? ማለት ለምዶብን እንጂ፥ የጠየቅነው ሰው ሰላም ባይሆን ሰላም የነሳውን ጉዳይ መርዳት በምንችልበት አቅም ለመርዳት ላንሄድ እንችላለን። ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌምና ከምርኮ ስለተረፉት አይሁድ ደህንነት ከጠየቀ በኋላ፥ ከወንድሞቹ የሰማው ምላሽ በእጅጉ ስሜቱንና ልቡን የሚጎዳ ነበር። “ይኸውልህ ነህምያ ኢየሩሳሌም ደህና አይደለችም። ቅጥሮቿ በሙሉ ፈርሰዋል። በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል። ከምርኮ የተረፉት የአይሁድ ቅሬታዎች ደግሞ በታላቅ መከራና ስድብ ውስጥ አሉ ብለው ይመልሱለታል። ነህምያ ይሄንን ዜና ከሰማ በኋላ ታዲያ የሰማው ዜና በእርሱ ዘንድ ተራ ጉዳይ አልነበረም። ቁጭ ብሎ እንዳለቀሰ እንዲሁም ትንሽ ቀን ሳይሆን በጣም ብዙ ቀን በሀዘን ውስጥ እንደቆየ ክፍሉን ስታነቡ በራሱ አንደበት የሚናገረው ነው። ታዲያ ነህምያ ብዙ ቀን ካዘነና ካለቀሰ በኋላ ልቡ ውስጥ የተፈጠረው ከባድ ሀዘን ሁለት ወሳኝ ነገሮችን ወደ ማድረግ እንደመራው ከዚህም የተነሳ በዘመኑ የነበረውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽሞ ሊያልፍ እንደቻለ እንመለከታለን።  ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ የሰማው ዜና ካደረሰበት ከባድ ሀዘን በኋላ፥ በመቀጠል የወሰደው እርምጃ በጾምና በጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት ወደ መፈለግ መሄድ እንደነበር በራሱ አንደበት እንዲህ በማለት ይናገራል።  “ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፥ እንዲህም አልሁ። አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥ እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል። እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም። አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ። እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው። እኔም ለንጉሡ ጠጅ አሳላፊው ነበርሁ።”  (መጽሀፈ ነህምያ ምእራፍ 1 ከቁጥር 4 ጀምሮ)  -ነህምያ ልቡ ውስጥ የተፈጠረው ከባድ ሀዘን ይዞት የሄደው ወደ ጾም ጸሎት ነው። ብዙ ጊዜ እኛ በተለያዩ ነገሮች ስናዝን ሀዘናችን ወደ ማጉረምረም ወይንም እግዚአብሔርን ወደ ማኩረፍ ይወስደን ይሆናል። ነህምያም ቢሆን እግዚአብሔር የተስፋ ምድር የሆነችውን ኢየሩሳሌምን እንዲሁም የኪዳን ህዝብ የሆነውን የአይሁድ ህዝብ እንዴት ይጥላል? እንዴትስ ለመፍረስ አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ወደ ማጉረምረም እኮ መሄድ ይችል ነበር። ሁልጊዜ ሀዘን ሲያጋጥመን፥ ያ ልባችን ውስጥ የተፈጠረው የሀዘን ስሜት ውሳኔያችንን ወዴት እንደሚመራው በጥንቃቄ ማሰብ አለብን። ሀዘን ወደ ሁለት ተቃራኒ አቅጣጫዎች ልባችንን ሊወስደው ይችላል። ወይ መፍትሄ ፍለጋ ወደ እግዚአብሔር ልባችንን ሊያቀርበው ይችላል። ወይንም ደግሞ በማጉረምረም እየሞላ ልባችንን ከእግዚአብሔር ሊያርቀው ይችላል። በየትኛውም ሀዘን ውስጥ ስናልፍ ውስጣችን የተፈጠረውን ስሜት ችላ ሳንል ትኩረት ሰጥተን ማዘንም ካለብን ማዘናችን ስህተት ባይሆንም፥ ይሄ ልባችን ውስጥ የተፈጠረው ሀዘን ግን ልባችንን ወዴት እንደሚወስደው በጥንቃቄ መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው ከባድ ሀዘን የሰዎችን የሕይወት አቅጣጫ ሊለውጥ የሚችለው። ነህምያ የነበረበት ሀዘን የወሰደው የእግዚአብሔርን ፊት ወደመፈለግ ነበር። የእርሱን እንዲሁም የአባቶቹን ሀጢያት በመናዘዝ መጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ካስተካከለ በኋላ፥ ጠጅ በማሳለፍ በሚያገለግለው በንጉሱ ፊት ምህረትና ሞገስ እንዲሰጠው አምላኩን ይለምናል።  ነህምያ ከጾመና ከጸለየ እንዲሁም ጉዳዩን ሁሉን ለሚችለው አምላክ ካስረከበ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ የወሰደው እርምጃ፥ የፈረሰውን ቅጥር ወደ መስራት ማሰብ ነበር። ይሄንን የፈረሰ ነገር ለመገንባት እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ ወደሚል ጥያቄ ነበር የገባው። ከጸለየ በኋላ እርሱ ማድረግ የሚችላቸውን ነገሮች ደግሞ ማሰብ ጀመረ። አንዳንድ ጊዜ እኛ በምንችለው አቅም መርዳት የምንችላቸው ችግሮች እያሉ፥ በጸሎት ሰበብ ቸል የምንላቸው ነገሮች አሉ። እግዚአብሔር እኮ የሚያደርገው እኛ የማንችላቸውን ከእኛ አቅም በላይ የሆኑትን ነገሮች ነው። የኢየሩሳሌምን ቅጥር መስራት እኮ እንዲያውም ነህምያ ብቻውን ማከናወን የሚችለው ነገር አልነበረም። የነህምያ እምነት ግን የሰማዩ አምላክ ያከናውንልናል እኛ ባሪያዎቹ ደግሞ ተነስተን እንሰራለን። የምንችለውን እንሰራለን፥ የእኛን ሀላፊነት እንወጣለን። እግዚአብሔር ደግሞ ያከናውነዋል፥ ከእኛ አቅም በላይ የሆነውን እርሱ ያደርገዋል ነበር እምነቱ። እግዚአብሔር እኛ መሄድ የምንችለውን ርቀት እንድንሄድ ይፈልጋል። ምክኒያቱ ደግሞ ክብሩን የሚገለጠው በእኛ አለመቻል ውስጥ ስለሆነ ነው።   -ይሄ የነህምያን ታሪክ ሳነብ አንድ በጣም የገረመኝ ነገር፥ እግዚአብሔር አንድም ቀን ለነህምያ ሂድና ቅጥሩን ስራ ብሎ ትእዛዝ ሲሰጠው አንመለከትም። ብዙ ጊዜ እኮ በቃሉ ላይ የተጻፉልንን የአባቶቻችንን ታሪክ ስንመለከት፥ የአብዛኞቹ አባቶቻችን ታሪክ የሚጀምረው እግዚአብሔር ወይ በድምጽ፣ ወይንም በሕልምና በራእይ አለዚያም ደግሞ ሰዎችን በመጠቀም እነዚህ አገልጋዮች ጋር መጥቶ የልቡን ሀሳብ ለእነርሱ ከመንገር ነው። ብዙ ጊዜ ነብያቶችና የእምነት አባቶች ጉዞ የሚጀምሩት የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰምተው ነው። አብርሀምን ብንመለከት፣ ሙሴን ብንመለከት፣ ኢያሱን ብንመለከት፣ አብዛኞቹንም ነብያቶች ብንመለከት፥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምተው ጉዞ የጀመሩ ወይንም ድምፁን እየሰሙ የጀመሩትን መንገድ የቀጠሉ ሰዎች ናቸው። የተለማመድነው እግዚአብሔር አባቶቻችንን በማዘዝ ሲልካቸው እነርሱ ደግሞ እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ነገሮች በመታዘዝ ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች ሲያደርጉ ነው። የነህምያን ታሪክ ለየት የሚያረገው፥ መፅሀፉን ጀምራችሁ እስከምትጨርሱ ድረስ እግዚአብሔር አንድም ቀን ወደ ነህምያ መጥቶ ይሄንን አድርግ ብሎ ሲያዘው አንመለከትም። እግዚአብሔር ታላቅና የኪዳን ምድር የሆነችውን አንድ ታላቅ ሀገር ኢየሩሳሌምን እንደገና ለማደስ ሲነሳ ከተጠቀመባቸው ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው ነህምያ። ነገር ግን አንድም ቀን እግዚአብሔር ወደ ነህምያ መጥቶ ይሄንን የልቡን ሀሳብ ሲያጫውተው አንመለከትም። ሌላው ቀርቶ ቅጥሩን በመገንባት ላይ እያለ እንኳን እግዚአብሔር መጥቶ በርታ ልጄ አይዞህ ሲለው አናነብም። እነ ጦቢያ እነ ሰንበላጥ ነህምያ የጀመረው መልካም ስራ ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሲሆኑ እራሱ እግዚአብሔር መጥቶ አይዞህ ብሎ ድምጽ ሲልክለት አንመለከትም።  ሙሉ መጽሐፉን ስታነቡ አንድም ጊዜ እግዚአብሔር ድምጹን ወደ ነህምያ አልላከም። ነገር ግን ነህምያ የኪዳን ምድር የሆነችውን የኢየሩሳሌምን ታላቅ ቅጥር ያደሰና የገነባ የፈረሰችውን የኪዳን ምድር እንደገና ለማቆም እግዚአብሔር ካስነሳቸውና ከተጠቀመባቸው ጥቂትና ታላላቅ ሰዎች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ነበር። እግዚአብሔር ታዲያ በነህምያ ዘመን ላይ ወደ ነበረው ታላቅ አገልግሎት እንዴት ነው የመራው ብለን ስንመለከት፥ በቃ በነህምያ ልብ ውስጥ ሸክምን ብቻ ነው ያስቀመጠው። እግዚአብሔር ጉዳዩን ሸክም አርጎ ልቡ ውስጥ አስቀመጠ። እግዚአብሔር በዘመኑ ወደነበረው ታላቅ አገልግሎት ነህምያን የመራው ልቡ ውስጥ ባስቀመጠው ሸክም ነበር። 

Article

ስኬት

Home Blog Book About Contact X Order Book ስኬት Audio ስኬት ስለሚለው ቃል ስናስብ መቼም ሁላችንም ልብ ውስጥ የሚመጡ ይሄን ይሄን ባሳካ ብለን በልባችን ውስጥ የምናስባቸው፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስኬቶች ይኖሩናል። ከዚያም በተጨማሪ ደግሞ በአካባቢያችን ላይ የምናውቃቸው ወይንም በsocial media ገጾቻችን እነሱ እንኳን ሳያውቁን እኛ የምናውቃቸውና የምንከተላቸው፣ በየቀኑ የሚያወጡትን ፎቶዎች እያየን የስኬት ምሳሌዎች ያረግናቸው ሰዎችም ይኖራሉ። ስኬት ለሁሉም ሰው የተለያየ ትርጉም ያለውና በህይወት ዋጋ ከምንሰጣቸው ነገሮች ጋር የተያያዘ ነገር ነው። ለአንዳንዱ በልፋቱ የሚያገኘው ደሞዝና ዋጋው ነው። ለሌላው ደግሞ ትምህርቱን ጨርሶ ያሰበውን ስራ መያዝ ማግባትና መውለድ ሊሆን ይችላል። ለሌላው ደግሞ አካባቢው ባሉ ሰዎች ወይንም በብዙሀኑ ዘንድ በሰራው ስራ እውቅናና ዝናን ማግኘት ሊሆን ይችላል። “ለእኔ በጤናና በሰላም ስራዬን ሰርቼ የቀን ለቀን ውሎዬን በሰላም ካለፍኩ ስኬት ነው” የሚሉ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሁሉ ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮች ምንም ክፋት የሌለባቸው፣ እንዲያውም በዚህች ምድር ላይ ስንኖር ሊያስፈልጉን የሚችሉና የምንጠቀምባቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ደግሞ ልክ እንደ አንድ ክርስቶስን በህይወቱ ለመከተል እንደወሰነ ሰው ሆነን ህይወትን ስናየው ከሌሎች ክርስቶስን ከማይከተሉ ሰዎች ለየት ያለ የስኬት ትርጉም ሊኖረን እንደሚገባ እናስተውላለን። ለመማር፣ ለማግባትና ለመውለድ የክርስቶስ ተከታዮች መሆን አይጠበቅብንም። እንዲያውም፣ ስኬትን በእነዚህ ነገሮች ከተረጎምነው፣ ከእኛ በላይ በብዙ እጥፍ የተሳካላቸው ብዙ በክርስቶስ ያልሆኑ ሰዎች በምድራችን ላይ አሉ። ታዲያ ከተጠራንበትና ነገሮችን በሙሉ ልንመዝንበት ከተሰጠን ህይወት አንጻር ስኬትን እንዴት እናየዋለን?  እኛ ስኬትን ለየት ባለ መንገድ እንድናየው የሚረዳን የውስጥ አይኖቻችን ተከፍተው ከዚህች አጭር 70 እና 80 አመት ቀጥሎ የሚጀምር ዘላለም የሚባል ቁጥር የማይወስነው ዘላለማዊ የሆነ ህይወት እንዳለ መረዳታችን ነው። አያችሁ ጌታን የማያውቁ ሰዎች ስኬትን የሚተረጉሙት አይናቸው ሊያይ እስከሚችለው 70 እና 80 አመት ርቀት ብቻ ነው። ህይወታቸውን የሚያቅዱት በዚህች ምድር ቆይታ ላይ ብቻ ተመስርተው ነው። ስለዚህ ስኬት ለእነሱ አብዛኛውን ጊዜ የተያያዘው፣ ከዚህች ምድር ምቾት ጋር ብቻ ነው። እኛ ግን ስኬትን የምናየው፣ ከዚህች በጣም አጭር የምድር ቆይታ አልፈን እንድናይ እግዚአብሄር በሰጠን ሰፊ እይታ ውስጥ ሆነን ነው። ስለዚህ በጣም የምንጨነቀው ለዚህች ምድር አጭር ቆይታችን አይደለም። ለዘላለም ነው። የእግዚአብሄርን ቃል በስፋት እያነበብን ስንመጣ፣ በቃሉ ውስጥ የእግዚአብሄርን ልብ እየተረዳነው እንመጣለን። ሀሳቡን እያወቅነው፣ ከሚናገራቸው ንግግሮች፣ ከሚሰጣቸው ምሳሌዎች፣ ደጋግሞ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ሀሳቦች፥ ዋጋ የሚሰጠው ምን ላይ እንደሆነ፣ የሚያተኩረው ምን ላይ እንደሆነ፣ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እየተረዳን ወይንም እያወቅነው እንመጣለን። ታዲያ እስከዛሬ ድረስ ካነበብነው ወይንም በስብከትና በትምህርት ከሰማነው አስተውለን ካየነው፥ እግዚአብሄር ከምንም ነገር በላይ፥ ትኩረት ወይንም ቅድሚያ የሚሰጠው ዘላለም ለሚባለውና ይህቺን አጭር የምድር ቆይታ ስንጨርስ ስለምንጀምረው ህይወት ነው። እግዚአብሄር ስሙ ወይንም መጠሪያው የዘላለም አምላክ፣ መንግስቱና ዙፋኑ የዘላለም፣ ምህረትና ፍቅሩ የዘላለም፣ ለእኛ የሰጠንም ህይወት የዘላለም ነው። ወንጌል በጣም አስፈላጊና የእግዚአብሄርን ልብ የያዘ ነገር የሆነው የሰዎችን የዘላለም አድራሻ ወይንም የዘላለም መኖሪያ የሚቀይር ነገር ስለሆነ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሄር የልቡ ትርታ ዘላለም ከሚለው ቃል ጋር በጣም የተሳሰረ ነው። ይሄ አሁን እየተነጋገርንበት ያለነውን ነገር የሚያጠናክርልንንና በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 18 ላይ ኢየሱስ ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ እስኪ አንዱን እንመልከት። አንድ ጊዜ ስለ ማመንዘር ትምህርት ሲሰጣቸው እንዲህ አለ። ቀኝ አይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት ሙሉ ሰውነትህ በገሀነም ከሚጣል፣ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሀልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፣ ሙሉ ሰውነትህ በገሀነም ከሚጣል  ይልቅ፥ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና አላቸው። አያችሁት የኢየሱስን እይታ። ብዙ ጊዜ እኛ ስንቀልድ እንኳን፥ በአይኔና በዚህ ሰው ቀልድ አላውቅም እያልን እንናገራለን። እውነት ነው አይን በጣም አስፈላጊ ከምንላቸው የሰውነት ክፍሎቻችን አንዱ ስለሆነ ነው። እንደ ኢየሱስ ንግግር ከሆነ ግን፥ በጣም አስፈላጊ ነው ከምንለው ከአይናችን በላይ ሌላ በጣም አስፈላጊ ነገር አለ። እሱም ደግሞ ዘላለማችንን የምናሳልፍበት ቦታ ነው። ኢየሱስ፥ ዘላለማዊ በሆነ እይታ ውስጥ ሆኖ ሲያየው፣ በምድር ላይ አስፈላጊ የምንለውን ነገር አተን ዘላለማችንን ከእርሱ ጋር ብናሳልፍ ነው ያተረፍነው። በምድር ላይ አስፈላጊ የምንለው ነገር ዘላለማችንን ካሳጣን የኢየሱስ ፍርድ ይሄ ነው። አውጥታችሁ ጣሉት ወይንም ቆርጣችሁ ጣሉት። በጣም ይጠቅመኛል ብለን የያዝነው ነገር፥ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ህብረት ካበላሸብን፣ አውጥተን ጥለነው እግዚአብሄርን ወይንም ዘላለማችንን በጥንቃቄ ብንጠብቀው ትልቅ ማስተዋል ነው። ከአይናችን በላይ ልንጠብቀውና ልንንከባከበው የሚገባን ነገር ቢኖር፥ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ህብረትና ዘላለማችንን ነው።  እግዚአብሄር ዘላለም ለሚባለው ህይወታችን የሚሰጠውን ቦታ በድርጊት ወይንም በስራ ካየንባቸው ነገሮች ዋነኛው፣ የእኛን የዘላለም አድራሻ ይቀይር ዘንድ፣ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር መላኩ ነው። መዳናችን፣ ኢየሱስ ለእኛ በመስቀል ላይ የሰራውን ስራ በማመን ብቻ ያገኘነው ስጦታ እንደሆነ እናውቃለን። ሁልጊዜ መርሳት የሌለብን ግን፣ ስጦታ የሆነው ለእኛ ብቻ እንጂ፣ ኢየሱስን ግን ያላስከፈለው ዋጋ አልነበረም። ነጻ ስጦታ የሆነው ለእኛ ብቻ ነው። ኢየሱስ ግን እያንዳንዱን የውርደት ጥግ ያየባቸው አሰቃቂ 33 አመታቶች ናቸው። እኛ ሰዎች ስለሆንን ለእኛ ሰው መሆን ቀላል ነው። መጽሀፉ ስለ ኢየሱስ ሲነግረን ግን በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ይለናል። ኢየሱስ ራሱን ማዋረድ የጀመረው፥ የሚሰቀልበት ሰአት ሲደርስ አይደለም። መስቀል ላይ ሲውል አይደለም። ራሱ ከምድር አፈር የሰራውን ሰው ለመሆን ሲወስን ነው። ራሱን ሰው ለማድረግ ከመወሰኑ አንስቶ፣ በምድር ላይ አለ በተባለው ውርደት ስቃይና መከራ ውስጥ የማለፉ ሚስጥር፥ እግዚአብሄር ዘላለም ለሚባለው ህይወት ያለውን ቦታ በትክክል ሊያስረዳን ይችላል። ክርስቶስ በምድር ላይ እያለ የተለያዩ ሰዎችን በመፈወስ፣ ከሰይጣን እስራት ነጻ በማውጣትና በተለያዩ መንገዶች የሰው ልጆችን የረዳ ቢሆንም ዋናው የመጣበት አላማ ግን የእኛን ዘላለም ለማስተካከል ነው። እንዲያውም በምድር ላይ የሰራቸው እያንዳንዱ ተአምራቶች ወደ ምድር የመጣበትን የዘላለም ህይወት ጉዳይ ሰዎች እንዲሰሙና እንዲረዱ ልባቸውን ለማግኘት የተጠቀመባቸው መንገዶቹ ነበሩ። ከኢየሱስ በሁዋላ የሀዋሪያቶችንም አገልግሎት ስታዩ፣ በሀዋሪያቶቹ እጅ እጅግ ብዙ ድንቅና ተአምራቶች ይደረጉ ነበር። የሚገርማችሁ ግን፥ የትኛውንም ተአምራት ስታነቡ፣ ከእያንዳንዱ ተአምራት በኋላ፥ ሰዎች ባዩት ነገር እየተደነቁ ልባቸውን ለእግዚአብሄር ይከፍቱ ነበር። ጆሮአቸውን ለወንጌል ይከፍቱ ነበር። ብዙዎች ጌታን ይቀበሉ ነበር። ብዙዎች ወደ እግዚአብሄር መንግስት ይጨመሩ ነበር። ሀዋሪያቶቹም በተአምራቱ የተከፈተውን የሰዎችን ልብ ተጠቅመው፣ ወዲያው ወንጌልን ይናገሩ ነበር። እግዚአብሄር በብዙ ድንቅና ተአምራት ቃሉን በመካከላቸው ያጸና ነበር። ዛሬም ምናልባት እግዚአብሄር በእጃችን ድንቅና ተአምራቶችን ያደርግ ይሆናል። እነዚህ ተአምራቶች ግን ለራሳችን የሰዎችን ትኩረት መሰብሰቢያዎች እንዳናረግ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ይልቁንም፥ ትንሽም ሆነ ትልቅ እግዚአብሄር በእኛ ተጠቅሞ የሰራው ነገር ካለና የሰዎችን ትኩረት እግዚአብሄር ከሰጠን፣ ቶሎ ብለን ስለ ተአምራት አድራጊው መናገር፥ እኛን ስለወደደበት ፍቅር የሰው ልጆችን ሁሉ ከሀጢያት በሽታ ለማዳን ልጁን መላኩን፣ የመዳኛ መንገዱ ደግሞ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን ለሰዎች መመስከር ይኖርብናል። የእግዚአብሄር የልቡ ትርታ ሰዎች ከጨጉዋራ በሽታ መፈወሳቸው አይደለም። ስለ ምድራዊ ፈውሶቻችን ግድ የሚለው አምላክ ቢሆንም፣ ዋናና ትልቁ አላማው ግን ሰዎችን ከሀጢያት በሽታና ዘላለማቸውን ከሚያሳልፉበት ከዘላለም ጨለማ አውጥቶ ወደ ዘላለም መንግስቱ ማስገባት ነው።  ታዲያ እግዚአብሄር ለዘላለም የሚሰጠው ቦታ እጅግ በጣም ትልቅ እንደሆነ ከተረዳን፣ ስኬት ከእግዚአብሄር እይታ አንጻር ምንድነው? ስኬት ከዘላለም አንጻር ሲታይ ወይንም፣ 70 እና 80  አመታቶችን አልፎ ማየት በሚችለው መነጽራችን ስናየው ምንድነው? እግዚአብሄር አንድን ሰው የተሳካ ህይወት ነበረው የሚለው ያ ሰው በምድር ላይ በተሰጠው ጥቂት ዘመናቶች ምን አይነት ህይወት ሲኖር ነው? ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ እንግዲህ፣ ከእኔ ተማሩ ያለው ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖረባቸው ስኬታማ አመታቶች በላይ ሌላ ሊያስተምረን የሚችል ነገር የለም። በተሰጠው በጣም አጭር አመታቶች እያንዳንዱን የተሰጡትን ጊዜያቶች በትክክል በመጠቀም ስኬታማ ሆኖ ያለፈና እኛም አሁን እየኖርን ላለነው ህይወት ትልቁ ምሳሌያችን፣ ክርስቶስ በምድር ላይ

Article

ስራ

Home Blog Book About Contact X Order Book ስራ Audio መቼም ለመዳናችን አንዳች ነገር አለማዋጣታችን እና እንዲሁ በጸጋ መዳናችን የሚገርም እና የሚደንቅ፥ የምንጊዜውም የልባችን ምስጋና፥ ሁልጊዜ ልባችን በእግዚአብሔር ፊት አመስጋኝ የሚሆንበት እውነት ነው። ደግሞ እኮ ትንሽ እንኳን ጽድቅ ተገኝቶብን ቢሆን ቅዱስ መጽሐፉም ለጻድቅ ሰው የሚሞት በጭንቅ ሊገኝ ይችላል እንደሚለው ነው። ለእንደ እኛ አይነት ሀጢያተኞች እና ተስፋ ለሌላቸው ሰዎች የሚሞት ግን በፍጹም አይገኝም። መቼም መዳን ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ሙታን የነበርነውን ሰዎች በፍቅሩ ሕያዋን ያደረገበት፣ የፍቅርን ሀይል መጨረሻው ጥጉን ያየንበት፣ እኛ ፍቅር ብለን ከምንጠራው ስሜት አልፎ ነፍሱን በመስጠት ድርጊቱ የፍቅርን ትርጉም እውነተኛ እና አይተን የማናውቀው ደረጃ ያደረሰበት፥ ከዚህ በፊት በአለም ተሰምቶም፣ ታይቶም ተደርጎም ያልታወቀ ፥ ከዚህም በኋላ የማይደረግ የአምላክ ጥበብ የተገለጠበት እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ ክስተት ነው። ምክኒያቱም ስለ ቀድሞ ታሪካችን ሲናገር፥ ከፍጥረታችሁ የቁጣ ልጆች ነበራችሁ፥ በበደላችሁና በሀጢያታችሁ ሙታን ነበራችሁ የተባልንበት ሙታን ሰፈር የእግዚአብሔር ፍቅር ሲመጣ፥ ምንም ተስፋ በሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የነበረ ሕዝብ ታላቅ እና አስደናቂ ብርሀን ሲያይ፥ ባሪያ ልጅ ተብሎ ያለፋበትን መንግስት ሲወርስ ቃላቶች መግለጥ ከሚችሉት በላይ ይደንቃል። ልክ እንደ አስቴር እኮ ነው የሆነው። ንጉሱ አስቴርን ስለወደዳት ብቻ ያለፋችበትን፣ ያላዋቀረችውን እና ያልደከመችበትን መንግስት እኩሌታውን እራሱ ቢሆን ጠይቂኝ ያስባለው እኮ ንጉሱ እሷን የወደደበት ፍቅር ብቻ ነው። እኛም ያለፋንበትን መንግስት ወራሾች የሆነው፥ እንዲሁ ስለወደደን ብቻ እንጂ ከእኛ ውስጥ አንዳችንም የተገባን ሆነን አይደለም። የእግዚአብሔርን ፍቅር፥ መንፈስ ቅዱስ እራሱ ለነፍሳችን ካላስረዳልን ልክ እንደ ሂሳብ አንድና አንድ ብለን በስጋ አይምሮአችን መረዳት እና መገመት የምንችለው ነገር አይደለም። ኢየሱስ አንድ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ያላቸው ነገር ትዝ አለኝ። በዮሐንስ ወንጌል መጽሐፍ ላይ እንዲህ አላቸው። “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፥ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፥ የሚመጣውንም ይነግራችኋል” አላቸው። አይገርምም ኢየሱስ በጊዜው ብዙ ነገሮችን ሊነግራቸው ቢፈልግም፥ ሊነግራችው የወደደውን ብዙ ነገር መሸከም የሚችሉበት አቅም አልነበራቸውም። የእግዚአብሔርን እውነት ለመሸከም እና ለመረዳት የእግዚአብሔር መንፈስ ያስፈልጋቸው ነበር።  እግዚአብሔር ልጁን ያውም አንድያ ልጁን ለዚያ አሰቃቂ የመስቀል ሞት መስጠቱ፥ ሰዎች ከዘላለም ሞት እና ጥፋት እንዲድኑ የፈለገበትን ከፍተኛ የፍላጎት መጠን ያመለክታል። ከእኛ ጥፋት ልጁን በሞት ውስጥ ማሳለፍን መረጠ። አሁንም ቢሆን ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ወዶ ስለ ሰዎች መዳን ይታገሳል። አምላክ መቼም ደግ ነው፥ በጣም ደግ ነው። ከዚህ በላይ ደግ መሆን አይችልም። ደግነቱን፣ መልካምነቱን፣ ፍቅሩን፣ ምህረቱን ሁሉ አንድ ላይ አርጎ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ አሳይቷል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ምህረት ማሳያ፣ የፍቅሩ መገለጫ፣ የመልካምነቱ ምልክት፥ የደግነቱ ምስክር ነው። እግዚአብሔር መልካም ነው እንዴ? ከተባለ፥ ይኸው ምልክቱ፥ የእግዚአብሔር መልካምነትና ፍቅር በተግባር የተገለጠበት ማረጋገጫ ምልክቱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ በእምነት ብቻ ያገኘነውን ይሄ ሁሉ ዘለዓለማዊ የሆነ የሕይወት በረከት እንዴት እንደ ቀላል ነገር እናየዋለን? በሰዎች “አታካብዱ ወይንም አትመናፈሱ” መባልን ፈርተን እንዴት ዝም ብሎ ተራ የሆነ ሕይወት እንኖራለን? እስከ ጥግ ሄዶ ለሞተልን አምላክ፥ እስከ ጥግ በቻልነው ሁሉ መኖር ነው እንጂ። በሰዎች ፊት እርቃኑን መስቀል ላይ ለዋለልን አምላክ፥ ማካበድም ከሆነ ማካበድ ነው እንጂ። ደግሞ ለእግዚአብሔር ያልተካበደ ሌላ ለማን ይካበዳል? ለእግዚአብሔር ያልሆነ ሕይወትስ ሌላ ለማን ይሆናል? ይሄንን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ የወደደን እና የሞተልን ይሄ አምላክ ደግሞ፥ እኛም ሁለንተናችንን ሰጥተን እስከ ጥግ ድረስ ስንወደውና ስንኖርለት ይደሰታል። በቃ እግዚአብሔር ነካ ነካ የሆነ ከላይ ከላይ የሆነ ነገር፣ እንዲያው ለነገሩ የሆነ ነገር አይመቸውም። ሙሉ ልባችንን ይፈልጋል፣ ሙሉ መሰጠታችንን ይጠይቃል፣ ሁለንተናችንን ይፈልጋል። በእውነተኛ እና ለእርሱ ዋጋ በሚከፍል ሕይወታችን ይደሰታል። መዳን እኛ ሳንለፋበት በእምነት ብቻ የተቀበልነው ሕይወት ሲሆን፥ ይሄ ያመንነው እምነት ግን አምኛለሁ ከሚል ቃል አልፎ በስራ እና በተግባር የሚገለጥ መሆኑን የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ ይናገራል። እምነት በስራ እና በድርጊት የሚገለጥ ነገር ነው። ያመነ ሰው ያመነውን፥ ያመነበትን ሕይወት ነው የሚኖረው። ለምሳሌ አንድን ሰው ለአንድ ሳምንት ቤቱ ሄዳችሁ ጥናት አድርጉበት ወይንም ገምግሙት ተብሎ ቢነገረን እና ሰውዬው ስለ ራሱ ምንም ነገር ባይነግረን፥ በየቀኑ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በማየት እምነቱን በትክክል ማወቅ እንችላለን። ይሄ ልንገመግመው የሄድነው ሰው በመስራት የሚያምን ሰው ከሆነ፥ በየቀኑ ተነስቶ በሰአቱ ስራ ሲሄድ እናየዋለን፥ ለምሳሌ በእስፖርት የሚያምን ሰው ከሆነ፥ ጂም ሲሄድ እና እስትፓርት ሲሰራ እናየዋለን፥ ጤንነቱን መጠበቅ እንዳለበት የሚያምን ሰው ከሆነ፥ ጤናማ ምግቦችን እየመረጠ ሲመገብ እናየዋለን፥ ገንዘቡን የሚቆጥብ ከሆነ፥ ሴቭ በማድረግ የሚያምን ነው እንደሆነ እንረዳለን። ስለ እምነቱ ሰውዬው ቃል ሳይናገር፥ ድርጊቶቹን ብቻ በመመልከት ልቡና እምነቱ ያለበትን ቦታ እንዲሁ መረዳት እና ማወቅ እንችላለን። ድርጊቶቹ በሙሉ እምነቶቹን የሚያመለክቱ ናቸው። ለምሳሌ ግን አንድ ሰው በመስራት አምናለሁ ብሎ እየተናገረ፥ ያለ ምንም ምክኒያት ስራውን እየተወ ቁጭ ብሎ ከዋለ፥ ይሄ ሰው በመስራት አምናለሁ ይላል እንጂ በመስራት አያምንም። እምነት እና ስራ የተለያዩ ነገሮች ሳይሆኑ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን የያእቆብ መልእክት ምእራፍ 1፡26 ላይ እንዲህ በማለት የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል። “ከነፍስ የተለየ ስጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከስራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” ይላል። በክርስቶስ አምናለሁ ያልን የዳንን ሰዎች፥ እምነታችን በድርጊቶቻችን ውስጥ ካልተገለጠ ወይንም እግዚአብሔር የጠራንን ሕይወት ካልኖርን ወይንም ቢያንስ ለመኖር ካልሞከርን የቱ ጋር ነው ያመነው? የተጠራነው እኮ ልዩ የሆነ ሕይወት እንድንኖር ነው። ለምሳሌ ኢትዮጲያ እንኖር በነበረ ሰአት የምንተዳደረው በኢትዮጲያ ህገ መንግስት ነበር። ልክ እዚህ ሀገር ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ግን ሙሉ በሙሉ የመንግስት ለውጥ ነው ያደረግነው። የሕገ መንግስት ለውጥ ነው ያደረግነው። አሁን እኛ ከኢትዮጲያ ውጪ የምንኖር ሰዎች፥ በኢትዮጲያ መንግስት አይደለም የምንተዳደረው። ከኢትዮጲያ ልዩ በሆነ መንግስት ስር ነን። የምንሆነው፥ የምንኖርበት ሀገር ባወጣው ህገ መንግስት ነው። እዚህ ሀገር ላይ ለመቆየት ከመረጥን፥ ህገ መንግስቱን መቀበል እና ተግባራዊ ማድረግ መብታችን ሳይሆን ግዴታችን ነው። እንዲያውም ከኢትዮጲያ ሀገር ወጥተን የሌላ ሀገር ዜጋ ለመሆን ዜግነት ስንጠይቅ እኮ፥ እጃችንን አንስተን ቃል እንድንገባ ያረጉናል። ህገ መንግስታቸውን እንድናከብር፥ ሀገራቸውን እንድንወድ እና እንድንጠብቅ። ጌታን ስንቀበል የህገ መንግስት ለውጥ ነው ያደረግነው። አዲስ መንግስት፣ አዲስ የሕይወት አካሄድ፣ አዲስ እርምጃ፣ አዲስ ኪዳን እና አዲስ ሕይወት። አሁን በዚህች አለም መንግስት አይደለም የምንተዳደረው፥ ለሰማያዊው መንግስት ዜግነት ጠይቀን ቃል ገብተን ዜጎች ሆነናል። የምንተዳደረው በድሮው መንግስት ስርዓት አይደለም። ዜግነት ባገኘንበት ሀገር ሕገ መንግስት ነው። ሕገ መንግስቱ ፈጽሞ ጨለማ ከሆነው እና ከኋላ ትተን ከመጣንበት ከዚህች አለም መንግስት የተለየ ነው፡፡ ፈጽሞ የተለየ የብርሀን መንግስት ነው። ይሄ መንግስት የቅድስና መንግስት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ኋይል እየተሞላን የድሮውን መንግስት ስራ በመተው እንዲሁም ስጋን እና ምኞቱን በመካድ ቅድስናን ተግባራዊ የምናረግበት፥ በድርጊቶቻችን በንግግሮቻችን በሀሳቦቻችን ሁሉ ሁለንተናችንን ሕያው እና ቅዱስ መስዋእት እያደረግን ለአምላካችን የምናቀርብበት፥ የሚጠሉንን ሁሉ የምንወድበት፣ የሚረግሙንን የምንመርቅበት፣ ለሚያሳድዱን እና ክፉ ስለሚያረጉብን ሰዎች የምንጸልይበት። የክርስቶስ ሕያው መንፈስ በእኛ ውስጥ አድሮ ፍሬ በማፍራት የክርስቶስን አይነት ሕይወት ለመኖር እርዳታን የምናገኝበት አስደናቂ መንግስት ነው።  ያዳነን ጸጋ እራሱ በዚያኛው ትተን በመጣንበት መንግስት ውስጥ ያለውን ሀጢያተኝነትን እና አለማዊ ምኞት ክደን ራሳችንን እየገዛን፣ በልክ እየኖርን፣ በጽድቅ እና እግዚአብሔርን በመምሰል መኖርን እየተማርን የአምላካችንን እና የመድሀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እንድንጠባበቅ የሚረዳን ጸጋ ነው። በ2ኛ ጴጥሮስ 1፡5 ላይ ሲናገር ካመናችሁ በኋላ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነታችሁ ላይ ደግሞ እውቀትን ጨምሩ፥ በእውቀት ላይ ደግሞ ራስን መግዛትን ጨምሩ፥ እራሳችሁን እየገዛችሁ ደግሞ መጽናትን ጨምሩ፥ በዚያ ላይ ደግሞ እግዚአብሔርን መምሰልን ጨምሩ፥ እግዚአብሔርን እየመሰላችሁ የወንድማማቾችን መዋደድ

Article

ሰላምና ደስታ

Home Blog Book About Contact X Order Book ሰላምና ደስታ Audio ዛሬ ገና ከእንቅልፌ ስነቃ ነው ውስጤ በደስታ የተሞላው። ፈገግ እያልኩኝ ነበር ቀኔን የጀመርኩት። እኔ መሳቅና መደሰትን ከእግዚአብሄር እንደ ተሰጡኝ በረከቶች ነው የምቆጥራቸው። እውነተኛ የልብ ደስታ የሚመጣው ከእግዚአብሄር ዘንድ ብቻ እንደሆነ ልቤ በብዙ ሁኔታዎች ውስጥ ተምሯል። አሁን ላይ አንድ የሰማሁት ቀልድ ካሳቀኝ፥ መሳቅ የቻልኩት ቀልዱ ስለሚያስቅ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄር የውስጥ ደስታን ስለሰጠኝ እንደሆነ ስለሚገባኝ፥ እግዚአብሄርን “አንተ እኮ ደስታ እና ሳቄ   ነህ”  እለዋለሁ። ሰው እውነተኛ የሆነውን ደስታ ከብዙ ነገሮች ውስጥ ይፈልጋል። በህይወቱ ስኬቶች ብሎ ያስቀመጣቸውን ነገሮችም ቢያገኝ ዘለቄታዊ የሆነ ደስታ የሚያገኝ ይመስለዋል። የእነዚህ ነገሮች መሳካት ግን ጊዜያዊ እንጂ ዘለቄታዊ ደስታና እርካታን ህይወታችን ላይ ሊያመጡ አይችሉም። ምድራዊ ደስታ በጣም አጭር ከመሆኑም በላይ፥ በምክኒያት ውስጥ ብቻ የሚሰራ ነው። አሁን እያወራን ያለነው ደስታ ግን በስኬቶቻችን ውስጥ የምናገኘው አይነት ደስታ አይደለም። እኛ ከምናረጋቸውና ከማናረጋቸው ነገሮች ጋርም ምንም አይነት ተያያዥነት የለውም። ይሄ አይነቱ ሰላምና ደስታ እኛ ምድር ላይ ስኬት ብለን ባስቀመጥናቸው ነገሮች ውስጥ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ፥ ስንት ተሳካላቸው የምንላቸው ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች ሰላም ማጣት ውስጥ እየገቡ ራሳቸውን አያጠፉም ነበር። ስንት ታዋቂና ዝነኛ ሰዎች የአይምሮ ውጥረት ውስጥ እየገቡ ራሳቸውን ላይ ከባባድ ነገሮችን አይፈጽሙም ነበር። ይሄ የምንነጋገረው ደስታ ግን፥ ለመደሰት የትኛውንም አይነት ነገር ሳናደርግ፥ እንዲሁ በልባችን ውስጥ የሚፈስና ከእግዚአብሄር ብቻ የሚሰጥ የእግዚአብሄር በረከት ነው። ይሄ አይነቱ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ መሳካትና አለመሳካት፣ መሆንና አለመሆን፣ ማግኘትና አለማግኘት የሚባሉት ነገሮች አያስቆሙትም። ከምክኒያቶቻችን ውጪ የሚሰራ አስደናቂ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው። እንደ ምድራዊው ደስታ ከውጪ የሚመጣ ሳይሆን፥ ከውስጣችን ልክ እንደ ውሀ ምንጭ የሚፈልቅ ስለሆነ፥ በህይወታችን ውስጥ የሚያልፉት የትኞቹም ከባባድ ፈተናዎች ሊያስቆሙት አይችሉም። ለዚህ ነው መፅሀፍ ቅዱሳችንን ስናነብ የእግዚአብሄር ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ ሆነው በምስጋናና በሀሴት እየተሞሉ የዘመሩት። ለዛ ነው በጣም ከባድ በሆኑ ችግሮች ውስጥ እያለፉ ስለ መንፈስ ቅዱስ ደስታ የጻፉልን። አንድ ሰው ህይወቱ በብዙ ውጫዊ ፈተናና መከራ ውስጥ እያለፈ፥ ይሄንን መከራ ከብዙ የመንፈስ ቅዱስ ሰላምና ደስታ ጋር ሊያልፈው ይችላል። ሌላ ሰው ደግሞ ከውጪ ያለውን ህይወቱን ስትመለከቱት በብዙ ስኬት ውስጥ ያለ የሚመስል፥ እናንተ የምትፈልጉት ነገሮች በሙሉ ስላለው ደስተኛ የሚመስላችሁ፥ ውስጡ ግን ሰላም በማጣት፣ በፍርሀትና በጭንቀት ማእበል ውስጥ የሚናወጥ ሰው ሆኖ ሊገኝ ይችላል።  እግዚአብሄር በደስታ ውስጥ እንድንኖር ይፈልጋል። ሲፈጥረን እራሱ እኮ የፈጠረን፥ ደስተኞች ሆነን እንኖር ዘንድ ነው። እግዚአብሄር አዳምና ሄዋንን የፈጠራቸው፥ በኤደን ገነት ውስጥ ያለውን ደስታ እያጣጣሙ በእርካታ እንዲኖሩ ነበር። ይሄንን ሀሴትና ደስታ የሞላበት ሕይወት የቀማቸው አለመታዘዝ ነው። ይሄንን ደስታ የቀማቸው ሀጢያት ነው። እኛ ታዲያ በክርስቶስ ኢየሱስ የምናምን ሰዎች ሁሉ፥ እግዚአብሄር በልጁ ውስጥ መልሶ ከሰጠን ስጦታዎች ውስጥ አንዱ የራሱን ሰላም ነው። እግዚአብሄር እውነተኛ ደስታን ያስቀመጠው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተልና የእርሱን ሀሳብ በመታዘዝ በምንሄድባቸው መንገዶች ውስጥ ነው፡፡ በኢሳይያስ መጽሀፍ ምእራፍ 9 ላይም ሲናገር፥ “በጨለማ የሄደ ህዝብ ብርሀን አየ። በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሀን ወጣላቸው” ካለ በኋላ፥ “ህዝብን አብዝተሀል። ደስታንም ጨምረህላቸዋል። በመከር ደስ እንደሚላቸው፣ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።” በማለት እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን የሰጠን፥ ከጨለማ ወደ ብርሀን ሊያሻግረን እንዲሁም በህይወታችን ላይ ደስታን ሊጨምርልን እንደሆነ ይናገራል። ኢየሱስም በአንድ ቦታ ላይ ሲናገር እንዲህ አለ። “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ደግሞ አለም እንደሚሰጠው አይነት አይደለም” አለ። ኢየሱስ የሰጠን የራሱን ሰላም ነው። ኢየሱስ ጋር ያለው ሰላም ሌላ፥ ለእኛ የሰጠን ሰላም ደግሞ ሌላ አይደለም። ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ብሎ የሰጠን ራሱጋ ያለውን ሰላም ነው። መንፈሳዊነትን ልክ እንደ ሀዘን ቤት የሚቆጥሩ፥ አርግና አታርግ ከሚለው ህግ ጋር በማያያዝ፥ ልክ እንደ ህግ መፈጸሚያ ቦታ ብቻ የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ። ይሄ ግን ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነው። እኛ እግዚአብሄርን ደስ ለማሰኘት የምንኖር ሰዎች ስንሆን፥ እግዚአብሄር በእኛ ደስ በተሰኘ ቁጥር፥ ደስታውን በመንፈስ ቅዱስ መልሶ በልባችን ውስጥ እንደሚያፈሰው መረዳት አለብን። እግዚአብሄር ተደሰተ ማለት እኛ ተደሰትን ማለት ነው። ምክኒያቱ ደግሞ እግዚአብሄር እራሱ በመንፈሱ በልባችን ውስጥ ስለሚኖር ነው። አንድ ክርስቲያን እኮ በሀጢያት ጎዳና ውስጥ ሲጓዝ ደስተኛ መሆን የሚያቅተው፥ ልቡ ከእግዚአብሄር ልብ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው። የእግዚአብሔር መቅደስ ፥ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለሆነ ነው። እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው ነገር ሁሉ ደስ ያሰኘዋል። የሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ያሳዝነዋል። የሚያስቆጣው ነገር ሁሉ ያስቆጣዋል። ስሜቶቹ በልቡ ከሚኖረው ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር የተያያዙ ናቸው። አንድ ሰው ግን ከእግዚአብሄር መንፈስ እንዲሁ በነጻ የሚሰጠውን የደስታ መንፈስ ካላወቀ፥ ደስታ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዴት ያውቃል? ሰው የመንፈስ ቅዱስን ደስታ ካልተለማመደ፥ በህይወቴ ተደስቼ አውቃለሁ ብሎ ቢያስብም፥ እውነተኛ ደስታ ምን አይነት ስሜት እንዳለው እንዴት ያውቃል? ይሄ እውነተኛ ደስታ፥ ከእግዚአብሄር ብቻ የሚመጣ ነገር እንደሆነ ሳይረዱ “እስኪ ፈታ ልበል” ብለው ሰዎች ፈታ ማለትን ከዚህች ክፉ አለም ሲፈልጉ ያሳዝኑኛል። ይቺ አለም እኮ በአንድ በኩል ብትፈታም በሌላ በኩል ደግሞ እያሰረች ነው። ሙሉ ለሙሉ የፈታን እግዚአብሄር ብቻ ነው። “የእግዚአብሔር መንግስት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።” (ሮሜ 14:17) ይሄ የእግዚአብሄር ደስታ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ አምነው የእግዚአብሄር ልጆች ለሆኑ ሁሉ እንዲያው በነጻ የተሰጠ ስጦታ ቢሆንም፥ በክርስቶስ አምነው የዳኑ ሁሉ ግን እግዚአብሄር በሰጠው የደስታ ሙላት ልክ ይኖራሉ ማለት አይደለም። ይሄንን የእግዚአብሄርን ነጻ ስጦታ ለመስረቅ በየእለቱ የሚሰማራ ጠላት ቢኖረንም፥ አብዛኞቻችን ግን ይሄንን የደስታ መንፈስ የምናገኝበትን ዋና የሆነ መንገድ ቸል ስንለው ይታያል። የዚህን እውነተኛ ደስታ ሚስጥር ግን መጽሀፍ ቅዱስ በመዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 45 ቁጥር 7 ላይ እንዲህ በማለት በግልጽ ጽፎልናል። “ፅድቅን ወደድህ፥ አመፃንም ጠላህ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሄር አምላክህ በደስታ ዘይት ቀባህ” በማለት በእውነተኛ ደስታ የመቀባት ሚስጥሮች ሁለት መሆናቸውን ይነግረናል። የመጀመሪያው ፅድቅን መውደድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አመጻን መጥላት ነው። ይሄ የደስታ ዘይት ብዙ ጊዜ ሰው እጁን ጭኖብን የምናገኘው ነገር አይደለም። ይልቁንም በእግዚአብሄር ፊት ትክክል በሆነ ሕይወት በመመላለስ ውስጥ ብቻ እግዚአብሔር በመንፈሱ በልባችን የሚያፈሰው አስደናቂ የሆነ የእግዚአብሔር ሀሳብ ነው። ጽድቅን መውደድ ማለት፥ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዛት መውደድ ማለት ነው። በህይወታችን ውስጥ የምንወስናቸውን ትንንሽም ሆነ ትልልቅ ውሳኔዎች በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ለማየት መሞከር፣ እንደ እግዚአብሄር ቃል የሆኑትን መንገዶች መከተል፣ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ጊዜ በማሳለፍና ያወቅነውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ መኖር ማለት ነው። አመጽን መጥላት ማለት ደግሞ፥ እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ነገሮች መራቅ ማለት ነው። በእግዚአብሄር ሕግና ትእዛዛት ውስጥ በመሄድ፣  አለም ልትሰጠው የማትችለው ሰላምና ደስታ አለ። በምሳሌ መጽሀፍ ምእራፍ ሶስት ላይ ሲናገር፥ “ልጄ ሆይ ህጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም እድሜ፣ ሰላምም ይጨምሩልሀል።” በማለት፥ የመታዘዝ ህይወታችን ሰላም በህይወታችን የሚጨመርበት መንገድ እንደሆነ የእግዚአብሄር ቃል በግልጽ ይናገራል። የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሁም በሕይወታችን ያለውን ሀሳቡን በመከተል መኖር፥  በ1ኛ ጢሞቴዎስ ምእራፍ 4 ላይ “እግዚአብሄርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ” በማለት እንደሚናገረው፥ በቀን ለቀን በምናደርጋቸው ትንንሽ ጉዳዮች ጀምረን እራሳችንን እያስለመድን የምንመጣው ነገር ነው። ይሄንን በመለማመድ ስንኖር፥  ጽድቅን በመውደድ ውስጥ ያለው የደስታ ዘይት ሳያቋርጥ በህይወታችን መስራት ይጀምራል። የብሉይ ኪዳን መጻህፍቶችን ስናነብ፥ እግዚአብሄር ለእስራኤል ህዝቦች ህጎቹንና ትእዛዞቹን በማክበርና እርሱን በመታዘዝ በሚሄዱባቸው መንገዶች ውስጥ ብዙ ሰላም መኖሩን፥ ባለመታዘዝ በሚሄዱባቸው መንገዶች ውስጥ ግን ድንጋጤ፣ ፍርሀትና ጭንቀት እንደሚያጋጥማቸው ይናገራል። “ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ እንቅፋትም የለባቸውም” (መዝሙረ ዳዊት 119:165) እኔም አንድ የክርስቶስ ተከታይና የእግዚአብሔርን መንገድ ለመከተል ከሚሞክሩ ክርስቲያን ሰዎች ውስጥ አንዷ እንደመሆኔ፥ ባለፉት ጥቂት አመታቶች ውስጥ እየተለማመድኩ

Article

ሩጫ

Home Blog Book About Contact X Order Book ሩጫ Audio በልጅነቴ በጣም ከምወዳቸው ነገሮች አንዱ ሩጫ ነበር። በአጭሩ፥ ቆመን እናውራ ከምትሉኝ እየሮጥን እናውራ ብትሉኝ ይቀለኝ ነበር። አንዳንዴማ ማዘር ሱቅ ስትልከኝ፥ ለመሮጥ ከመቸኮሌ የተነሳ የምገዛውን ነገር በሙሉ ተናግራ እስክትጨርስ ለመስማት የሚሆን ትእግስት አልነበረኝም። እሷ ተናግራ ሳትጨርስ እኔ ሮጬ ሱቁ ጋር ደርሻለሁ። ግዢ ያለችኝን ነገሮች በትክክል ስላልሰማሁ ተመልሼ ስመጣ፥ ማዘር እዛው ቦታ ጋር ቆማ እየጠበቀችኝ ነው። ያው ወይ እገረፋለሁ ወይንም ደግሞ ከቻልኩ ለጊዜው ሮጬ በማምለጥ ቅጣቱን ወደ ማታ አራዝመዋለሁ። እነ ቀነኒሳ ሲሮጡ ማየትማ ነፍሴ ነበር። ሲሮጡ ፊታቸው ላይ የነበረው የድካም ስሜት እስካሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። መቼም ያንን ሁሉ ኪሎ ሜትር ያለ ምንም እረፍት መሮጥ እጅግ አድካሚና ብዙ ትእግስት የሚጠይቅ እንደሆነ ግልፅ ነው። ትልቁ ደስታና ያቺ ትንሿ ሰፈራችን በጩኸት የምትሞላው ግን ልክ የተመደበላቸውን ኪሎ ሜትር ጨርሰው ሲገቡና ሲያሸንፉ ነው። በደስታ የሚያለቅሱ ሰዎች እራሱ ነበሩ። ግማሹ ይዘላል፥ ግማሹ ይጮሀል፥ ሰው ሁሉ ልቡ ውስጥ ያለው ደስታ ሁን እንደሚለው ስለሚሆን፥ ቤቱ ልዩ በሆነ የደስታ ስሜት ይሞላ ነበር።  ምድራዊውን የጨዋታ ሩጫ መጨረስ እንዲህ የሚያስደስት ከሆነ፥ የዘላለም አክሊል የሚያስገኝልንን መንፈሳዊ ሩጫ ጨርሶ መግባት እንዴት የሚያስደስት ይሆን? ጳውሎስ ልክ እንደ ቀነኒሳ የራሱን ሩጫ ከጨረሰ በሗላ የተናገረው ነገር ትዝ አለኝ።  “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሀይማኖትን ጠብቄያለሁ ወደፊት የፅድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል። ይህንም ፃድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል። ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም” (2ኛ ጤሞ 4፡7)  ብዙ ጊዜ የእግዚአብሄርን ቃል ስታዩት፥ በምድር ላይ ያለንን የክርስትና ህይወት ከሩጫ ጋር እያወዳደረ ያስተምረናል። በዚህ ምድር ስንኖር የተመደበልን መንፈሳዊ ሩጫ አለ። ይሄ ሩጫ አንዳንድ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሁላችንን በክርስቶስ አምነን የዳነውን ሁሉ የሚመለከት ነው። አላማው ደግሞ በትእግስት፥ በፅናት፥ በሙሉ ትኩረት፥ ኢየሱስን በማየት ሮጦ መጨረስ ነው። ስለዚህ ስኬታማ ነን የሚባለው ይሄንን የተመደበልንን ሩጫ ሮጠን ጨርሰን ስንገባ ነው። ክርስቶስን በማመን የጀመርነው ህይወት፣ ልክ እንደ ሩጫ መነሻም መድረሻም አለው። ለዘላለም አንሮጥም። ትንሽ ብቻ ሮጠን፣ ዘላለም እናርፋለን። ሯጭ፣ መድረሻው ላይ የሚጠብቀውን ሽልማት እያሰበ ድካሙንና የሚከፍለውን ዋጋ ሁሉ እንደሚታገስ፣ ሩጫቸውን በትእግስትና በጽናት ለሚጨርሱ ሰዎች፥ እግዚአብሄር ያዘጋጀው ዘላለማዊ አክሊል አለ። ይሄ ሩጫ በዚህ ምድር ላይ በምንኖረው ኑሮ፣ እግዚአብሄርን ለመታዘዝና ደስ የሚያሰኘውን ህይወት ለመኖር በምንከፍለው መስዋእትነት ይመሰላል። አሁን ያለነው ሩጫ ላይ ነው። መንገድ ላይ ነን። ወደ ዘላለማዊ አክሊላችን የሚያደርሰን መንገድ ላይ ነን።  እንግዲህ ስለ መንፈሳዊ ሩጫ ስናስብ አላማው ሮጦ መጨረስ ይሁን እንጂ፥ የጀመረ ሁሉ ግን ይጨርሳል ማለት አይደለም። ብዙ ጊዜ ሩጫን ስታዩት የሚጀምሩት በጣም ብዙዎች ቢሆኑም የሚጨርሱት ግን ጥቂቶች ናቸው። የእስራኤልን ልጆች ታሪክ እንደ ምሳሌ ብናነሳ፥ መንፈሳዊውን ጉዞ የጀመሩት ከ600 ሺህ የበለጡ ሰዎች ቢሆኑም ከጀመሩት ውስጥ የጨረሱት ግን 2 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ታዲያ የጀመርነውን ይሄ የከበረና የዘላለም አክሊል የሚያስገኝልንን ሩጫ ለመጨረስ፥ የራሱን ሩጫ የጨረሰው ጳውሎስ ከመከረን ጠቃሚ ምክሮች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት። “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብ 12፡1-2)  1፥ ሸክምን ማስወገድ፦ እንግዲህ ሯጮችን ስናይ፥ ሲሮጡ ምንም የሚሸከሙት ሸክም የለም። ባዶ እጃቸውን ናቸው። አለባበሳቸውንም ስናይ፥ ጋቢ ለብሶ ወይንም ደግሞ ሙሉ ሱፍ ልብስ በቆዳ ጫማ አርጎ የሚሮጥ ሯጭ አይተን አናውቅም። በተቻላቸው መጠን ለሩጫው ይረዳቸው ዘንድ ሰውነታቸው ላይ ያለውን ሸክም ያቀሉታል። ሀጢያት ሩጫን የማዘግየት አልፎም ደግሞ አቋርጠን እንድንወጣ የማድረግ አቅም አለው። አቋርጠን መውጣት ስል፥ ከቤተክርስቲያን መቅረትንና ከክርስትና ህይወት መውጣትን ብቻ ሳይሆን፥ እዚሁ እግዚአብሄር ቤት ውስጥ እየተመላለስን ነገር ግን በትክክለኛው መንፈሳዊ ሩጫ ላይ ላንኖር እንደምንችል ማሰብም ጥሩ ነው። ምክኒያቱም ቤተክርስቲያን ውስጥ የምንሰባሰበው እንደ እኛ ከሚሮጡ ጋር እርስ በእርስ ለመበረታታት፥ ለሩጫችን የሚያስፈልገንን ፀጋ ለመካፈል፥ እንዲሁም የህብረት አምልኮን ለማድረግ እንጂ እግዚአብሄር የእያንዳንዳችንን የህይወት አካሄድ ወይንም ሩጫ የሚመዝነው በግል ነው። ስለዚህ ሩጫችንን የማስቆም ሀይል ስላለው፥ ከሀጢያትና ወደዛ ከሚወስዱን መንገዶች መራቅ የጀመርነውን ሩጫ ለመጨረስ በጣም ወሳኝ ነገር ነው ይለናል ጳውሎስ።  ሌሎች ነገሮች ደግሞ አሉ ሀጢያት ያልሆኑ ነገር ግን ከተመደበልን ሩጫ አንፃር ስናያቸው ሸክም የሆኑና ምንም ጥቅም የሌላቸው። ፀሀፊውም ሲፅፍ “ሸክምን ሁሉ፥ ቶሎም የሚከበንን ሀጢያት”  ብሎ የከፋፈለበት ምክኒያት አለው። በመንፈሳዊ ህይወታችን እያደግን ስንመጣ “ይሄ ነገር ሀጢያት ነው ወይንስ ሀጢያት አይደለም” ከሚል አስተሳሰብ አልፈን “ለጀመርኩት ሩጫ ይጠቅማል ወይንስ አይጠቅምም” ወደሚለው አስተሳሰብ ውስጥ እናድጋለን። ጳውሎስ አንድ ቦታ ላይ ሲናገር “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” እንዳለ፥ የተፈቀደልን ነገር ሁሉ የሚጠቅም ላይሆን ይችላል። ያንን የምንወስነው ከተመደበልን የመንፈሳዊ ሩጫ አንፃር ነው። አንዳንድ ነገሮች ሀጢያት አይደሉም ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ማስተዋል ውስጥ ስናያቸው ሸክሞች ናቸው። ሩጫችንን የማዘግየት አልፎም የማስቆም አቅም ሊኖራቸው ይችላል።  2፥ እይታን ማስተካከል፡- የሯጭ ሌላኛው ባህሪው፥ ለሚያጨበጭቡለት ሰዎች በየመንገዱ እየቆመ ምስጋና አያቀርብም። ለሚተቹትና ለሚነቅፉትም ሰዎች ቆሞ ራሱን አያብራራም። መሀል መሀል ላይ እየቆመ ድካሙንና ስሜቱን ለሰዎች ለማስረዳት አይሞክርም። ወደ ግራና ወደ ቀኝ ዞር ዞር እያለም የከተማውንና የተፈጥሮውን ውበት አያደንቅም። የእሱ አላማ እና ሙሉ ትኩረት ወደ ፊት ብቻ ነው። ሙሉ ልቡ ያለው መጨረሻ ላይ የሚጠብቀው ሽልማት ላይ ነው። በዚህ የመንፈሳዊ ሩጫ ውስጥ ጳውሎስ ከሚመክረን በጣም ጠቃሚ ምክሮች ውስጥ አንዱ እይታችንን በዙሪያችን ካሉት ሰዎችና ነገሮች ላይ አንስተን የእምነታችን ራስና ፈፃሚ የሆነው ክርስቶስ ላይ እንድናደርግ ነው። የምናየው ነገር ሩጫችንን የማበርታትም የማድከምም አቅም አለው። በሚገጥሙን ከባባድ የህይወት ፈተናዎች ላይ በፈተና የፀናውን ክርስቶስን ማየትና ማሰብ የፅናትን አቅም ይሰጠናል። አይኖቻችንን በዙሪያችን ካሉት ነገሮች ላይ አንስተን በክርስቶስ ውስጥ የምናገኘውን ዘላለማዊ ደስታና አክሊል ማየት፥ የምናልፍበትን ጊዜያዊ መከራ እንድንታገስ ይረዳናል። የክርስቶስን ህይወትና አገልግሎቶች ማጥናት አላማ ተኮሮች ያደርገናል። በዙሪያችን በሚሆኑት ነገሮች ተፅእኖ ስር ወድቀንም ሩጫችንን እንዳናቆም ይረዳናል።  “Our true success in this life is being able to fulfill the purpose we were created for!” Icon-facebook Youtube Instagram for the Kingdom through Christ ! Scroll to top Blog Book About Contact ©2026, Hana Elias. All Rights Reserved Blog Book About Contact

Article

ሩት

Home Blog Book About Contact X Order Book ሩት Audio ስራ በሌለኝና በእረፍት ቀናቶቼ ማድረግ ከምወዳቸው ነገሮች አንዱ፥ በጠዋት ተነስቶ ውሀ ዳር ያለ ፓርክ በመሄድ ቀለል ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ ነው። እንዴት አንደሚያዝናናኝ እንዴት ብዬ ልንገራችሁ!  በተለይ፥ በበጋና አየሩ ሞቃታማ በሆነባቸው ጊዜያቶች፥ የማለዳው ጸሀይ ነፋሻማ ከሆነው ተስማሚ አየርና በዙሪያዬ ከማያቸው የተለያዩ የተፈጥሮ ውጤቶች ጋር ተደምሮ፥ በደስታ ብዛት ሩጪ ሩጪ ስለሚለኝ ያሰብኩትን ቀላል የእግር ጉዞ ወደ ሩጫ የቀየርኩባቸው ጊዜያቶች ጥቂቶች የሚባሉ አይደሉም። የተፈጥሮ ውጤቶች መንፈሴን እያደሱ አዲስነትን ይሰጡኛል። የእግር ጉዞ ማድረግ፥ እየሄዱ ማሰብ፥ ለራሴ ጊዜ መስጠት፣ ውስጤን ማዳመጥ፣ በተቻለኝ አቅም መመለስ የምችላቸውን የልቤን ጥያቄዎች መመለስ፣ ያልቻልኳቸውን ደግሞ የእግዚአብሄር መንፈስ መልስ እንዲሰጥልኝ መጠየቅ። እነዚህ ከራሴ ጋር የማሳልፋቸው ጊዜያቶች፥ በተለያየ መንገድ ህይወቴን ሲጠቅሙት አይቻለሁ። ብዙ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ወስኜባቸዋለሁ። ዝምታዬን አዳምጬባቸዋለሁ። ልቤን አስተካክዬባቸዋለሁ። የእግዚአብሄር መንፈስ ሲገስጸኝ ሲመክረኝና ሲያጽናናኝ ደግሞ ሰምቼባቸዋለሁ። እናንተስ በእረፍት ቀናቶቻችሁ ማድረግ የምትወዱት ምንድነው? በዛሬው ጽሁፋችን፣ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ስላለች፥ በዚህ ወቅት አብዝቼ ስለማስባትና ስለምደነቅባት፥ እንዲሁም ብዙ ነገሮችን ለግል ህይወቴ ስለተማርኩባት አንዲት ሴት እንድናወራ አስቤያለሁ። ሩት። ሞአባዊት ሴት ናት።  በጣም ከሚገርሙኝና በብዙ ምሳሌነት ከምናነሳቸው ሴቶች መካከል አንዷ ናት። የህይወትዋን አካሄድ ሳየ፡ በተለያዩ ነገሮችዋ እደነቃለሁ። ምንም ከመሆን ተነስታ፣ ትውልድን የሚያልፍና ዘላለም የሚወራ ታሪክ ውስጥ መግባትዋ፥ ኪዳን ከሌለው ዘር ውስጥ መጥታ፥ የኪዳን ዘር ውስጥ መግባትዋ፣ ባልዋን ከማጣት ተነስታ ቦኤዝ ጋር መድረሷ፣ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ኢየሱስ እንኳን ሲነገር የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ተብሎ የተነገረለትንና እንደ እግዚአብሄር ልብ የሆነውን የዳዊትን ቅድመ አያት በመውለድ የነገስታት ዘር ውስጥ መግባትዋ፣ ከዳዊት ዘር ከይሁዳ ነገድ የመጣው ደግሞ የክርስቶስ የዘር ሀረግ ውስጥ የመግባትን ማእረግ ማግኘትዋ ይገርመኛል። መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥም በስማቸው መጽሀፍ ከተጻፈላቸው ሁለት ሴቶች መካከል አንዷ ሩት ናት። የኪዳን ህዝብ የሆነችው ኑሀሚን ብትሆንም፣ መጽሀፉ የተሰየመው ግን በሩት ስም መሆኑና መጽሀፉ የእሷ ታሪክ ላይ ማተኮሩም እንዲሁ ይገርመኛል። ታዲያ ያገኘችውን ይሄንን ሁሉ ክብርና ማእረግ ስናይ፥ ሩት ማናት? ምን አይነት ሰው ናት? እምነቶችዋ ምንድናቸው? ባህሪዋ ምን አይነት ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም። ብዙ ጊዜ የሩትንና የአስቴርን መጽሀፍ ሴቶች ብቻ በብዛት ሲያተኩሩበት ይታያል። ነገር ግን የሩትና የአስቴር ታሪክ ለሴቶች ብቻ፥ የነ ዳዊት የነ ሙሴና የነ ጳውሎስ ታሪክ ደግሞ ለወንዶች ብቻ ትምህርት ለመሆን የተጻፈ ሳይሆን፣ በእርግጥ ከጾታ ልዩነታችን በተወሰነ መልኩ የምንወሰዳቸው ለየት ያሉ ትምህርቶች ቢኖሩም፥ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ከተጻፉት ሰዎች በሙሉ ካስተዋል፣ ለሁላችን የሚሆኑ ብዙ ትምህርቶች አሉ።  ታሪኩን ስናነበው፥ አቤሜሌክ የተባለው ሰው፥ በሀገሩ ከነበረው ረሀብ የተነሳ፥ ሚስቱን ኑሀሚንንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ ወደ ሞአብ ሀገር እንደሄደ በመናገር ይጀምራል። ወደ ሞአብ ምድር ሄዶ ብዙም ሳይቆይ ነው ይሄ ሰው እንደሞተ መጽሀፉ የሚነግረን። ይሄ ሰው በሞአብ ምድር መሞቱን እንዲሁም ደግሞ የኑሀሚን ሁለት ወንዶች ልጆችዋ ሚስቶችን አግብተው አስር አመታቶችን ከኖሩ በኋላ እነሱም እንዲሁ መሞታቸውንና ኑሀሚን የሁለቱ ወንዶች ልጆችዋ ሚስቶች ከነበሩት ከሩትና ከኦርፋ ጋር መቅረትዋን በመናገር ታሪኩ ይቀጥላል። ኑሀሚን ታዲያ ባልዋንና ሁለቱን ልጆችዋን ካጣች በኋላ ወደ ህዝቧ ልትመለስ ስትወስን፥ እነዚህ የልጆችዋ ሚስቶች የነበሩት ሁለት ወጣት ሴቶች፥ ከእርስዋ ጋር ለመሄድ ጥያቄ አቅርበውላት ነበር። “አይሆንም ልጆቼ ከዚህ በኋላ ምን ቀረ ብላችሁ ነው የምትከተሉኝ? እኔ ዛሬ እንኳን አግብቼ ወንዶች ልጆችን ብወልድ ለእናንተ ባል ለመሆን ይደርሳሉ? ይልቅ እዚሁ ህዝባችሁ ውስጥ ነው ትንሽም ቢሆን የማግባት ተስፋ ያላችሁ:: እኔን ትታችሁ የራሳችሁን ህይወት ብትቀጥሉ ነው የሚያዋጣችሁ” ብትላቸው ኦርፋ እውነት እኮ ነው። እኔ በወጣትነቴ ባሌን ያጣሁ ሰው ነኝ:: ከዚህ በኋላ ደግሞ እድሜዬ ሳያልፍ ቶሎ ብዬ ማግባትና መውለድ ይኖርብኛል ብላ በማሰብና ከኑሀሚን ሀሳብ ጋር በመስማማት የደህና ሁኚ ሰላምታ ሰጠቻት። ይህቺ ሴት ምንም ያጠፋችው ጥፋት የለም። ትክክል ናት። ለእሷ፥ የማታውቀው እንግዳ ሀገርና ህዝብ ውስጥ በመሄድ ጊዜዋን ከምታባክን፥ ጊዜዋ ሳያልፍባት ቶሎ ብላ አብሯት ሊሆን የሚችል ጥሩ ሰውን ከምታውቀውና ዘመንዋን ሙሉ ከኖረችበት ህዝብ መካከል መፈለግን ነው ይሻላል ብላ ያሰበችው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፥ አብዛኖቻችን በእነዚህ ወጣቶች ቦታ ብንሆን፣ ከኦርፋ የተለየ ነገር የምናረግ አይመስለኝም። ሩትን እኮ ልዩ ያረጋት ሰው የማይመርጠውን መንገድ መምረጧ ነው። የማታውቀው ምድር ለመሄድ፣ በዘመንዋ የማታውቀውን አምላክ ለመከተል፣ ተወልዳ ካደገችበትና ቋንቋውን፣ ህብረተሰቡን፣ ባህሉን ከለመደችው ምድር ወጥታ፥ አንዲት ተስፋዋ የጨለመባት የመሰለችን ሴት ተከትላ በመሄድ ከአዲስ ህብረተሰብና ከአዲስ ባህል ጋር ለመላመድ መወሰንዋ እኮ ነው ልዩ ያረጋት። አንዳንድ ሰዎች ግን አይገርሟችሁም? ሪስክ ለመውሰድ ደፋሮች ናቸው። ለየት ያሉ ምርጫዎች አሏቸው። የብዙሀኑ ምርጫ ተጽእኖ አያሳድርባቸውም። ያመኑበትንም ነገር ለማድረግ ብቻቸውን መቆም አይፈሩም። በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ትልልቅ ደረጃ ሲደርሱ የምናያቸው እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ነው። አልበርት አንስታይን ያለው አንድ አባባል ትዝ አለኝ። “ተመሳሳይ ነገር እያደረክ የተለየ ውጤት አትጠብቅ ይል ነበር”። ኦርፋ ኑሀሚንን የመሰናበቻ ሰላምታ ስትሰጣት፥ ሩት ግን ተጠጋቻት ይለናል መጽሀፉ። አንድ ተስፋ የሌላትን ሴት ለመከተል ወሰነች። ህዝቧንና አምላኳን ተቀብላ ለመከተል ወሰነች። የሚገርመው እኮ ደግሞ ሩት የኑሀሚንን አምላክ እግዚአብሄርን ለመከተል የወሰነችው እግዚአብሄር ኑሀሚንን ሲያትረፈርፋት፣ ሲሰጣት፣ ሲባርካት አይታ እንኳን ቢሆን ብዙም ላይገርመን ይችላል። ሩት ያየችው ኑሀሚን ባልዋ ሲሞት ልጆችዋ ሲሞቱና ብቻዋን ስትቀር ነው። ሩት ከኑሀሚን የምትሰማው፣ “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛል” ስትል ነው። ታዲያ እንዴት የኑሀሚንን አምላክ እግዚአብሄርን ለመከተል አቅም አገኘች? እግዚአብሄርን የሚያስከትል ምን ተስፋ አየች? ምን ብርሀን አየች? እኛ እኮ ታሪኩን በሙሉ አንብበን ስላወቅነው ነው ብዙም የማይገርመን። ሩት ህይወትዋ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ምንም የማታውቅ አንድ ምስኪን ሴት ነበረች። ኑሀሚንን ለመከተል የወሰነችው፥ ዛሬ ላይ እኛ የታሪኳን መጨረሻ አውቀን እንደተቀመጥነው፥ ህይወትዋ የሚሄድበትን አካሄድ አውቃ፥ ቦኤዝን እንደምታገባ፣ የዳዊትን ቅድመ አያት ኢዮቤድን እንደምትወልድ፣ የክርስቶስ ዘር ውስጥ እንደምትቀላቀል አውቃ ህይወትዋን ቀድማ አይታ እኮ አይደለም። አንድ ነገር ውስጥ እኮ የሆነ ተስፋ ይዞ መግባትም አንድ ነገር ነው። ህይወቷ በምን ሁኔታ እንደሚጠናቀቅ ፍንጭ እንኳን ሳይኖራት ዝም ብላ ተስፋ የሌላት የመሰለችን ሴት ለመከተል የወሰነች ሰው ናት። ምናልባትም አካባቢዋ ላይ ያሉ ሰዎች “ሩት ምን ነካሽ አንቺ ቆይ? እኔ በእውነት ዝም ብለሽ የማይሆን መንገድ ስትሄጂ እያየሁሽ ዝም ማለት አላስችል ስላለኝ ነው የምመክርሽ:: ለምን ስለራስሽ ህይወት ግን አታስቢም? የሴት ልጅ እድሜ እኮ ቆሞ አይጠብቅም። እስካሁን ልጅ እንኳን አልወለድሽም። እዚሁ ከምታቂው ባህሉን እምነቱን ከለመድሽው ህዝብ መካከል የሚሆንሽን ሰው ብትፈልጊ ነው የሚሻልሽ” የሚሏትም የሚጠፉ አይመስለኝም። ለነገሩ ቢሏትም እኮ ትክክል ናቸው። እውነታቸውን ነው:: ደግሞም ምንም ቢናገሩ ለእሷ ካላቸው ቀና አስተሳሰብ ተነስተው ነው። ግን እኮ አንዳንድ ምክሮች ጥሩ ቢሆኑም፥ ከትልቁ ከእግዚአብሄር ፕሮግራም ጋር ግን አብረው የሚሄዱ አይደሉም። የእኛን ስኬትና ምቾት ብቻ ያካተቱ በህይወታችን ላይ ያለውን ትልልቅ የእግዚአብሄር ሀሳቦች ግን ያላካተቱ፥ ከሰው እይታ አንጻር ሲታዩ ትክክል የሆኑ፣ ከእግዚአብሄር እይታ ደግሞ ሲታዩ ሚዛን የማይደፉ ብዙ ምክሮች አሉ።  ሩት ሁሉንም ነገር ትታ ከኑሀሚን ጋር ለመሄድ ቆራጥ ሀሳቧን ተናገረች። አንድ ውሳኔ ከወሰነች ንቅንቅ የሚያረጋት የለም። “ኑሀሚን ወደ ህዝቤ እንድመለስ አታስገድጂኝ:: ህዝብሽ ህዝቤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል። በምትሞቺበት በዚያ እሞታለሁ። በምትቀበሪበትም በዚያ እቀበራለሁ። ከሞት በቀር እኔና አንቺን የሚለየን የለም በማለት አንድ ወንድና ሴት ለመጋባት ሲወስኑ የሚገቡትን አንድ ከባድ ኪዳን ነው የገባችላት። አዎ ብዙ ተስፋ አላቸው ካልናቸው ሰዎች ጋር ቃል መገባባት ምናልባት ቀላል ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ከአንድ ተስፋዋ ከጨለመባት፥ ብቻዋን ከቀረችና ምንም ጥቅም ከማናገኝባት ደካማ ሴት ጋር ግን ካንቺ ጋር እሞታለሁ ብሎ ኪዳን መግባት ማንነትን ይጠይቃል። በቃሎችዋ ውስጥ ማንነትዋ ይታያል። ማን እንደሆነች ያስታውቅባታል። ለነገሩ

Article

ምስጋና

Home Blog Book About Contact X Order Book ምስጋና Audio በህይወቴ ላይ በተለያዩ ስሜቶች ውስጥ ያለፍኩባቸው የተለያዩ ቀናቶች አሉ። በጣም ደስተኛ የሆንኩባቸው፥ እግዚአብሄር ግን እንዴት መልካም አምላክ ነው ያልኩባቸው፣ የዘመርኩባቸውና እግዚአብሄርን የባረኩባቸው ብዙ ቀናቶች ህይወቴ ላይ አሉ። ልክ እንደዚሁ ደግሞ፥ በጣም ያዘንኩባቸው፥ ልቤ የተሰበረባቸው፣ እግዚአብሄርን ለምን ብዬ ለመጠየቅ የተነሳሁባቸውና ልቤ ከምስጋና እጅግ በጣም የራቀባቸው ቀናቶችም ህይወቴ ላይ ነበሩ። የእነዚህ ቀናቶች ክብደት፥ እግዚአብሄርን ብዙ ነገር እንድለው አርገውኝ ያውቃሉ። “እኔ አንተን የማመልክ፣ አንተን የምከተል፣ አንተን የማገለግል ሰው ሆኜ፥ ለምን በዚህ ውስጥ ታሳልፈኛለህ? እኔ እንደዚህ ይሄ ነገር ሲከብደኝ፥ ለምን አንድ ነገር አታረግም?” ብዬ እግዚአብሄር ላይ እንደ መናደድም፥ እንደ መቆጣትም፥ እንደ ማኩረፍም እሆንና ለመጸለይ ብንበረከክም፥ ስላኮረፍኩ እግዚአብሄርን ዘግቼው ከተንበረከኩበት የተነሳሁባቸው ቀናቶች ነበሩ። ለምንድነው እግዚአብሄር ላይ እናደድና፣ አኮርፍ የነበረው ብዬ እነዚህ ስሜቶቼ ውስጥ ያሉትን እውነተኛ ምክኒያቶች ስመረምራቸው፥ አንድ ዋና ምክኒያት አገኘሁ። ያገኘሁት ዋና ምክኒያት ይሄ ነበር። ህይወቴ ያልፍ ለነበረባቸው ከባድ ነገሮች ተጠያቂ የማደርገው፥ እግዚአብሄርን ነበር። ህይወቴ ላይ ላለፉት ነገሮች እግዚአብሄርን ተጠያቂ ማድረጌን በተያያዝኩባቸው በእነዚያ ወቅቶች ነበር አንድ አካላዊ ህመም ወይም Physical pain ውስጥ አልፍ የነበረው። ህመሙ ለህይወቴ የሚያሰጋ ባይሆንም፥ የህመሙ መጠን ትንሽ ከፍ ያለ ስለነበር፥ ድሮ አደርጋቸው የነበሩትን አንዳንድ ነገሮች ማድረግ አለመቻሌን፥ እንዲሁም ከነገሩ ጋር የተያያዙትን አንዳንድ ነገሮች በማሰብ ስሜታዊ ሆኜ በእግዚአብሄር ፊት በነበርኩበት በአንድ አመሻሽ ላይ ነበር አንድ ህይወቴን የቀየረ መረዳት ወደ መንፈሴ ውስጥ የፈሰሰው። ይሄ የተሸከምኩት ስጋ ምድራዊ ነው። ይታመማል፣ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፣ በህመምና በስቃይ እንዲሁም በመከራ ውስጥ ሊያልፍ ተፈርዶበታል። ጌታን ማምለኬ፣ እግዚአብሄርን በህይወቴ መከተሌ ላለመታመሜ ወይንም በችግሮች ውስጥ ላለማለፌ ምክኒያት ሊሆን አይችልም። ኢየሱስ እራሱ እንኳን በምድር ሳላችሁ መከራ አለባችሁ በማለት፣ ይህቺ ምድር ከመከራ ውጪ ልትሆን እንደማትችል ግልጽ አድርጎ ተናግሯል። ህመም በዚህች ምድር ስኖር ላልፍ የምችልበት አንዱ ነገር ነው። ህይወት በዚህች ምድር ከመከራ ውጪ ልትሆን አትችልም። ከችግር ነጻ ልትሆን አትችልም። ከችግር፣ ከመከራና ስቃይ ነጻ የምሆነው ዘላለማዊ ቤቴ ስሄድ እዛ ስደርስ ነው። አሁን ምድር ላይ ነኝ ያለሁት። ስለዚህ ይሄ የተሸከምኩት ስጋ ላይ ህመም፣ ችግርና መከራ ሊደርስበት ይችላል። ይሄ ሁላችንም የምናውቀውና አዲስ ያልሆነ ነገር ይሁን እንጂ በደምብ እራሳችንን ስንመረምር፥ እኔን እራሴንም ጨምሮ የብዙ ማጉረምረማችንና እግዚአብሄርን ለምን ብለን የመጠየቃችን ምክኒያት ይሄንን እውነት መረዳት ባለብን መጠን አለመረዳታችን ነው። ለምሳሌ አንድ ትምህርት ቤት ለመግባትና ለመማር የፈለገ ሰው፥ ትምህርት የሚጠይቃቸውን ነገሮች ስለሚያውቅ፥ የቤት ስራ በተሰጠው ቁጥር፣ የሚያጠናው ብዙ የትምህርት ቤት ስራዎች በተሰጡት ቁጥር፣ ፈተና በተፈተነ ቁጥር ግራ አይገባውም። ምክኒያቱም ትምህርት ለመጀመር ሲያስብ እነዚህ ነገሮች ከትምህርቱ ጋር አብረው ሊመጡ የሚችሉ ህጎች እንደሆኑ አውቆና አይምሮውን አዘጋጅቶ ስለሚገባበት ነው። ስለ ትምህርት እና ትምህርት ስለሚጠይቃቸው ነገሮች ምንም መረጃ የሌለው ሰው ግን ከላይ የዘረዘርናቸው ትምህርቱ የሚጠይቃቸው ነገሮች በመጡበት ሰዐት ግራ ነው የሚገባው። የትምህርት ህግ አልገባውም። ያልጠበቃቸው ነገሮች ስለሆኑ፣ አይምሮውን ያላዘጋጀባቸው ነገሮች ስለሆኑ ይናደዳል፣ ይበሳጫል፣ ያጉረመርማል የሚሰጡትንም ፈተናዎች ይወድቃል። በትምህርቱም ፈጽሞ ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ምክኒያቱ ምንድነው? የትምህርት ህጉ ስላልገባውና ለህጉ አይምሮውን ስላላዘጋጀ ነው። ከአዳምና ሄዋን ውድቀት በኋላ፥ እኛ የሰው ልጆች ወደዚህች መከራ ወደ ሞላባት ምድር መጥተናል። የመጣንባት ምድር መከራ ያለባት፣ ህመም ያለባት፣ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ያሉባት ምድር ናት። ደስ የሚለው ነገር ጊዜያዊ መቆያችን እንጂ ዘላለም መኖሪያችን አለመሆኗ ነው። እግዚአብሄር ስሙ ይባረክ፣ ልጁን ኢየሱስን ወደ ምድር ልኮ የዘላለማችንን አድራሻ ቀይሮታል። ችግሮቻችንን እና መከራዎቻችንን አጭር አድርጎታል። ዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር እንድንኖር፥ የእንደገና አምላክ እንደገና እድል ሰጥቶናል። ይህቺ ለጊዜው የመጣንባት ምድር ግን የመከራ ምድር ናት። አጭርና መከራ የሞላባት ምድር ናት። ስለዚህ በዚህች ምድር ላይ ቁጭ ብለን፥ ምቾትን አልጋ በአልጋ መሆንን የምንጠብቅ ከሆንን በሚገጥመን ችግር ቁጥር እግዚአብሄርን ለምን ለማለት የምንቸኩልና ለማማረር የምንፈጥን ሰዎች ነው የምንሆነው። ስለዚህ ይሄ ምድራዊ መከራ በራሳችን አለመታዘዝ ምክኒያት የመጣንባት የዚህች ምድር ሁኔታ እንጂ የስቃያችን፣ የመከራችን የህመማችን ምክኒያቱ እግዚአብሄር አይደለም። እግዚአብሄር የምናልፍበት የትኛውም ምድራዊ ችግር ምክኒያት አይደለም። በመከራዎቻችንና በስቃዮቻችን ውስጥ በፍጹም የእግዚአብሄር ትብብር የለበትም። እንዲያውም እግዚአብሄር ችግራቸው የእኔ ጥፋት አይደለም፥ ችግራቸው ውስጥ እጄ የለበትም ብሎ አንድም ጊዜ እኛን ከመርዳት እጁን አጣጥፎ የተቀመጠበት ቀን የለም። ባለፍንባቸው ጥቂትም ሆነ ብዙ ዘመናቶች፥ እኛን ለመርዳት እግዚአብሄር እጁን ያልዘረጋበት ጊዜ የለም። በምናልፍበት ሁሉ ውስጥ በገዛ ፍቃዱና ፍቅሩ አብሮን እያለፈ የእሳቱን ሀይል በማጥፋት እንዳያቃጥለን ያረግልናል እንጂ። በውሀ ውስጥ ስናልፍ፥ በገዛ ፍቃዱ አብሮን እያለፈ ውሀው እንዳያሰጥመን ይጠብቀናል እንጂ። መቼ ነው እግዚአብሄር የእኛን ጉዳይ ተመልክቶ፥ አያገባኝም ብሎ የተቀመጠው? በመከራዎቻችን ሁሉ የጸጋውን ብርታት በህይወታችን  እያሳለፈ፥ እስከዛሬ ድረስ አጽንቶ አቆመን እንጂ:: እንዲያውም ችግሮች ከምንችለው በላይ ሆነው ወደ ህይወታችን እንዳይመጡና ከምንችለው በላይ እንዳንፈተን ለመፍቀድ ህይወታችን ላይ ጣልቃ ይገባል እንጂ! ይህቺ ምድር የምታመጣብንን መከራ ከእኛ አቅም ጋር በማስተያየት እየመጠነና እየለካ እምነታችንን ለማሳደግ፣ ትእግስታችንን ለመጨመር፣ ስለ እርሱ ያለንን እውቀት ለማሳደግ እየተጠቀመ እየመጣ ላለው የዘላለም ክብር ተስፋ እኛን ያዘጋጅበታል እንጂ፥ የሚጠቅሙንን ባህሪያቶች በእኛ ውስጥ ያሳድግበታል እንጂ፣ ልጁን ኢየሱስን በእኛ ውስጥ ይስልበታል እንጂ፥ የራሳቸው ጉዳይ ነው አያገባኝም ብሎ ገለል ያለው መቼ ነው? እግዚአብሄር በፍጹም የመከራችን አካል አይደለም።  አሁን ጽፌ ከማነብላችሁ በላይ፥ ይሄ መረዳት ችግሮችንና መከራዎችን የማይበት አመለካከቴን የማስተካከልና የመቀየር ከፍተኛ የሆነ ሀይል ነበረው። በዚህች ምድር ስኖር ለማልፍበት ለየትኛውም ችግር እግዚአብሄር ምክኒያቱ እንዳልሆነ፣ የእኔ የትኛውም ጉዳት ውስጥ የእግዚአብሄር እጅ እንደሌለበት መረዳቴ “ለምን” የሚለውን ትልቅ ጥያቄ ከልቤ ውስጥ ሻረልኝ። አሁን ላይ ነገሮች ሲከብዱኝ ባለቅስ እንኳን፣ የእግዚአብሄርን እርዳታ ፈልጌ እንጂ እርዳታን ከእሱ እየለመንኩ እንጂ እግዚአብሄርን ተጠያቂ አድርጌው አይደለም። እግዚአብሄርን ለብቻው፥ የራሴን ችግሮች ለብቻ ለያይቼ ነው የማያቸው። ይሄ መረዳት ልቤን ቀየረልኝ። ምስጋናዬን ቋሚ አደረገልኝ። በሁሉ አመስግኑ የሚለውን ቃል ህያውነት ከህይወቴ ጋር አገናኘልኝ። በዚህ መረዳት ውስጥ ስገባ ነው አንኮንዲሽናል ምስጋና ወደማቀርብበት አለም ጥቂት የተጠጋሁት። ይሄንን መረዳት ሳገኘው ነው “እግዚአብሄር መልካም ነው” የሚለው ቃል በደምብ የገባኝና “መልካም ነህ” ብዬ የምዘምረው ዝማሬ በእግዚአብሄር ፊት እውነተኛ የሆነልኝ። እኔ ወደ ከፍታ ስወጣም መልካም እንደሆነ፥ ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ስወርድም መልካም አምላክ እንደሆነ፣ እግዚአብሄር ፍጹም ርህራሄን የተሞላ፣ ፍጹም ለሰው ልጆች ሁሉ የሚራራ፣ ለሚለምኑት ሁሉ የእርዳታ እጁን አለመዘርጋት የማይችል፣ የሚለመን፣ ሰዎችን ሁሉ መርዳት የሚወድ፣ መልካምነትን የተሞላና መልካምነት ማንነቱ የሆነ አምላክ እንደሆነ የገባኝ:: ከዚያ ነገር በኋላ፥ የማልፍበትን ሁሉ በዚህች ምድር ላይ በመኖሬ ላልፍበት የሚገባኝ ነገር እንደሆነ ነው የምቆጥረው። ከዚያ ግን ምህረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ተብሎ እንደተጻፈው፣ በማልፍበት ሁሉ የእግዚአብሄርን እርዳታ፣ የእግዚአብሄርን ጸጋ እለምናለሁ። ሲረዳኝ ታዲያ እግዚአብሄር እኔን የመርዳት ግዴታ እንደሌለበት ለነፍሴ እነግራታለሁ። እግዚአብሄር እኔን የመረዳት ግዴታ እንዳለበት አላስብም። እንኳን እኔን የመርዳት እርዳኝ ብዬ የለመንኩትን ጸሎት እራሱ የመስማት ግዴታ የለበትም። የመመለስ ግዴታም የለበትም። የሚሰማኝ፣ የሚመልስልኝ፣ የሚረዳኝ፣ ግዴታ ስላለበት አይደለም:: በማንነቱ ምህረትን የተሞላ፣ ትእግስትን የተሞላ፣ የፍቅር አምላክ ስለሆነ ብቻ ነው። የሚሰማኝ፣ የሚመልስልኝ፣ የሚወደኝ፣ ልጁ ያደረገኝ ይሄንን ሁሉ የማድረግ ግዴታ ስለነበረበት አይደለም። በማንነቱ የፍቅር አምላክ ስለሆነ ነው። ከራሱ መልካም ተነሳሽነት ብቻ ነው። የማድረግ ግዴታ የሌለበትን ነገሮች ማድረጉና በዚህ ውስጥ የማይገባኝን ነገር ለእኔ መስጠቱ ልቤን በምስጋና ይሞላልኛል። ምስጋናዬንም ብዙ ያደርግልኛል።   የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ ታዲያ ምንድነው? በህይወታችን እያለፍን ያለንባቸው ከባባድ ጉዳዮች ቢኖሩ፣ ወይንም መንገዳችን ላይ ቢመጡ እነዚህን ነገሮች እግዚአብሄርን ደስ በሚያሰኝ ልብ፣ የእግዚአብሄርን መልካምነት ባለመጠራጠር፣ ባለማጉረምረምና በትክክለኛው መንገድ የእግዚአብሄርን ጸጋና እርዳታ ብቻ እየለመንን ከእውነተኛ ምስጋና

Article

ምርጫ

Home Blog Book About Contact X Order Book ምርጫ Audio መቼም ህይወታችን የየቀን ምርጫዎቻችን ውጤት መሆኑን ብዙዎቻችን እናስተውላለን። አብዛኞቹ ህይወታችን ላይ ያሉት ነገሮች፥ የእኛ ምርጫ ውጤቶች ናቸው። ለምሳሌ የምንሰራበትን መስሪያ ቤት መርጠን ማመልከቻ አስገብተን ነው የገባነው። የምሄድበትን ቤተክርስቲያን መርጠን ነው የምንሄደው። ቀናችንን በምን አይነት ሁኔታ እንደምናሳልፍ፣ የት መሄድ እንዳለብን፣ ከማን ጋር ጓደኛ መሆን እንዳለብን ጨምሮ በጣም ብዙ ህይወታችን ላይ ያሉት ነገሮች፥ የእኛ ምርጫ ውጤቶች ናቸው። እግዚአብሄርም የሰው ልጆችን ምርጫ የሚያከብር አምላክ ሲሆን፥ የተሰጠንን ነጻ የምርጫ ፈቃድ ተጠቅመን መልካም ምርጫዎችን እንመርጥ ዘንድ ይመራናል። ምርጫችንን ተጠቅመን ህይወታችንን ወደ ተሻለ ቦታ እንድንወስድና ከክፉ ሁሉ እንድናመልጥ፥ ከፊታችን ካሉት ምርጫዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ውጤት እያስቀደመ ይናገራል። ዘዳግም 30 ላይ ሙሴ ከመሞቱ በፊት የእስራኤልን ህዝብ እየደጋገመ የእግዚአብሄርን ሀሳብ መምረጥ እንዳለባቸው እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃቸው ነበር።  “በሕይወትም እንድትኖር እንድትበዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ።” ይልና ቁጥር 19 እና 20 ላይ፥ “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።” በማለት ትክክለኛውን ምርጫ እንዲመርጡ ሙሴ ህዝቡን ያበረታታ ነበር።    ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ ስትመለከቱ፥ እግዚአብሄር በኤደን ገነት ውስጥ ስላለችው የሞት ዛፍ ለአዳም ነገረው እንጂ እጁን ጠምዝዞ እንዲበላ አላደረገውም። እጁን ጠምዝዞ እንዳይበላም አላደረገውም። የዛፉን ፍሬ ለመብላትም ሆነ ላለመብላት በልቡ ውስጥ ያስቀመጠው ምርጫ ብቻ ነው። ምርጫ በጣም ፖወር ፉል ነው። ለዚህ ነው በሕይወታችን የምንመርጠውን እያንዳንዱን ምርጫ በማስተዋል ማድረግ ያለብን። እግዚአብሔር ለአዳም ምርጫን ከሰጠው በሁዋላ፥ ፍሬውን ለመብላት ከመረጠ፥ ከዚህ ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ውድቀትና ሞት ገና ሳይበላ በፊት አስቀድሞ ነግሮታል። እግዚአብሄር የአዳምንና የሄዋንን እጅ ጠምዝዞ ፍሬውን እንዳይበሉ ቢያደርግ ኖሮ፥ የፈቃድ አምላክ አይባልም ነበር። እግዚአብሔር ለአዳም ፍቅሩን የገለጠው እጁን ጠምዝዞ በኤደን ገነት ውስጥ የተተከለውን ፍሬ እንዳይበላ በማድረግ ሳይሆን፥ ፍሬውን ቢበላ የሚመጣውን ውጤት በመናገር ነው። እግዚአብሔር ሊመርጥ የሚችለውን ምርጫ ውጤት ሳይናገር ዝም ይል ዘንድ ልቡ ውስጥ ያለው ፍቅር አላስቻለውም። ዛሬም እንደገና የሰው ልጆችን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ መንግስቱ ለማስገባት የሰዎችን እጅ አይጠመዝዝም። ይልቁንም በእኛ በብርሀን ልጆች እየተጠቀመ ለዓለም ሁሉ ኢየሱስን ምረጡ እያለ ይጮሀል። ኢየሱስን ብትመርጡ የዘላለምን ህይወት ታገኛላችሁ። ሌላኛው ምርጫችሁ ግን የዘላለምን ሞት ያመጣባችሁዋል እያለ ዓለም ልጁን ትመርጥ ዘንድ ለዓለም ወንጌልን ይመሰክራል።   ያው ሁላችንም እንደምናውቀው፥ አዳም የመረጠው ምርጫ ሞትን አምጥቶበታል፥ ከእግዚአብሄር መለየትን አምጥቶበታል። አይገርማችሁም ግን አዳም ፍሬውን ከበላ በኋላ ይሄንን የተሳሳተ ምርጫ የመረጥኩት የሰጠኸኝ ሚስት አሳስታኝ ነው፥ ሄዋን ደግሞ እባቡ አሳስቶኝ ነው ብላ ምክኒያት ብታቀርብም፥ እግዚአብሄር የትኛውንም አይነት ምክኒያት አልተቀበለም። አይገርማችሁም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስንተላለፍ እኮ በፊቱ ቀርበን ምህረትን ከመለመን ውጪ ለስህተታችን የምንደረድራቸው ምክኒያቶችና ሰበቦች እግዚአብሄርን ሊያሳምኑት አይችሉም። የመረጥነውን ምርጫ ውጤት በደስታም ሆነ በጸጋ የመቀበል ግዴታ አለብን። አዳምና ሄዋን የዛሬ ስንትና ስንት ሺህ አመት በመረጡት ምርጫ ዛሬ የዓለም ህዝብ በሙሉ ዋጋ እየከፈለ ነው። አንዳንድ ምርጫዎች ጉዳታቸው ለረጅም ጊዜ በሕይወታችን የሚቀጥል ሊሆን ይችላል። “እነርሱ ባጠፉት እኔ ለምን እቀጣለሁ?” ብለን የምናስብ ሰዎች ካለን፥ እኛም በእነርሱ ቦታ ብንሆን ከእነርሱ የተለየ ምርጫ ልንመርጥ እንደማንችል እርግጠኞች ሁኑ። ምክኒያቱ ደግሞ እኛም ልክ እንደ እነርሱ ሰዎች የሆንን፣ ልክ እንደ እነርሱ ስሜት ያለን፣ የስጋ ምኞትና አምሮት ያለን፣ ልክ እንደ እነርሱ በጠላት የምንታለን ሰዎች ስለሆንን ነው። እግዚአብሄር ግን ደግ ነው። እኛ ባጠፋነው የራሱን ልጅ ኢየሱስን ዋጋ አስከፍሎታል። እንዲያውም እኮ “እነርሱ ባጠፉት እኔ ለምን እቀጣለሁ?” ማለት የነበረበት ክርስቶስ ነበረ። ምክኒያቱም እርሱ ምን አጠፋ? ለመታዘዝ መርጦ የሰው ልጆችን ሆነ እንጂ፥ ከመጀመሪያ መች የሰው ልጅ ነበረ? እርሱ ጻድቅ በመሆኑ፥ ስለ ሀጢያት ዋጋ የመክፈል ግዴታ መች ደረሰበት? ግድ ቢለው ፍቅር ብቻ እንጂ፥ ማን ስለ ሀጢያት ሊከሰው ይችላል? ይሄ ሁሉ ፍቅርና ምህረት ለማይገባን ለእኛ የበዛው የእግዚአብሄር ፍቅር እጅግ በጣም አስደናቂ ነው። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የከፈለውን ዋጋ በማመን ብቻ የዘላለምን ህይወት አገኘን። ድጋሚ ወደ እግዚአብሄር መንግስት ለመግባት እድል ተሰጠን። ምህረት ተደረገልን፥ እንደገና ተባልን። እግዚአብሄር ጽድቁን፣ ቅድስናውን፣ መንግስቱን አወረሰን። አካፈለን። ምህረቱ በእኛ ላይ ተገለጠ። ታዲያ ግን እዚህ ጋር ልብ ማለት ያለብን፥ በስጋ እስከምንሞት ወይንም ወደ ጌታ እስከምንሄድ ድረስ ይህቺ የተጣልንባት የመከራ ምድር ልታመጣብን የምትችለውን መከራ መቀበላችን የግድ እንደሆነ ነው። ኢየሱስ ዋጋ የከፈለው ከሞት በኋላ ያለውን ዘላለማችንን ለማስተካከል ነው እንጂ ምድራዊ ህይወታችን አልጋ በአልጋ እንዲሆን አይደለም። አዳምና ሄዋን የሰሩት ሀጢያት ምህረትን አግኝቶ የዘላለምን ህይወት ለመውረስ ድጋሚ እድል ቢሰጠንም፥ አንዴ በሰራነው ሀጢያት ምክኒያት የተጣልንባትን የዚህችን ምድር መከራ መቀበላችን ግን ግድ ነው። ሀጢያት ሁልጊዜም ቢሆን የሚያመጣብን መዘዝ አለው። አሁን ሀጢያት ሰርቼ በኋላ ንሰሀ እገባለሁ የሚባል ነገር የለም። አዎ እግዚአብሄርማ እኮ ይቅር ይላል። በዘራነው የሀጢያት ዘር ውስጥ ያለውን ዋጋ ግን መክፈላችን አይቀርም።            ይሄንን ለመረዳት እግዚአብሄር እንደ ልቤ ያለውንና ታላቅ የእግዚአብሄር ሰው የሆነውን የዳዊትን ህይወት ማጥናት በቂ ነው። ዳዊት እጅግ በጣም በእግዚአብሄር የተወደደ ሰው ነው። በዘመኑ ሁሉ የእግዚአብሄርን ሀሳብ አገልግሎ እንዳለፈ የተጻፈለት፥ እግዚአብሄርን አብዝቶ የሚወድና የሚፈልግ አስደናቂ ልብ የተሰጠው ሰው ነበር። ምንም በእግዚአብሄር እጅግ በጣም የተወደደ ትልቅ ሰው ቢሆንም ግን፥ የዳዊትን አጠቃላይ ህይወት ስትመለከቱ፥ ሕይወቱ በጣም በብዙ ፈተናዎችና መከራዎች የተሞላ የሰልፍ ሕይወት ነበር። በተለይ ደግሞ የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሀፍን ስትመለከቱ፥ የንግስና ወንበሩን ትቶ እስኪሸሽ ድረስ ያደረሱት ከባባድ ፈተናዎች በህይወቱ አልፈው እንደነበር ትገነዘባላችሁ። እነዚህ እጅግ በጣም ብዙ ዋጋ ያስከፈሉት ፈተናዎች፥ ዳዊት ከሰው ሚስት ጋር በመተኛቱና ንጹህ ሰው በማስገደሉ በሰራው ሀጢያት ምክኒያት ህይወቱ ላይ የመጡ የሀጢያት ዘር ውጤቶች ነበሩ። ዳዊት ምንም በእግዚአብሄር የተወደደ ሰው ቢሆንም፥ በሰራው ሀጢያት የበቀሉትን ዘሮች ማጨዱ ግን አልቀረም። የዳዊትን ህይወት በጣም ካከበዱት ነገሮች ውስጥ አንዱ፥ በዘራው የሀጢያት ዘር ምክኒያት የበቀሉት የመከራ ውጤቶች ነበሩ። ሀጢያት ልክ እንደ ዘር ነው፥ ጊዜ ጠብቆ ይበቅላል። ብዙ ዋጋንም ያስከፍላል። መጽሀፍ ቅዱስ በዘፍጥረት መጽሀፍ ምእራፍ 8 ቁጥር 22 ላይ ሲናገር “በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።” በማለት የምዘራው ጥሩም ሆነ መጥፎ ዘር ጊዜ ጠብቆ እንደሚበቅልና ይሄ ህግ አንዴ በእግዚአብሄር የተወሰነ እንዲሁም ሊቀየር የማይችል ህግ እንደሆነ ይናገራል።  ዳዊት ስለሰራው ሀጢያትና እግዚአብሔርን ስለበደለበት በደል ንሰሀ በመግባት ወዲያውኑ የእግዚአብሔርን ምህረት አግኝቷል። እግዚአብሔር ምህረት አድርጎለት፥ ሀጢያቱን በሙሉ ይቅር ብሎታል። በሰራው ሀጢያት ውስጥ የተመደበውን ቅጣት ግን ሳይከፍል ፈጽሞ ከዚህች ምድር አላለፈም። እግዚአብሄር ምህረቱ ብዙ የሆነ መሀሪና ታጋሽ አምላክ ነው። ምህረቱን ለለመኑት ሁሉ አይከለክልም። እኛን በመማርና ይቅር በማለት ይደሰታል። ስለሰራናቸው ሀጢያቶች ግን የምንከፍላቸው ዋጋዎች አሉ። በዚህ በስጋችን የሰራናቸውን ሀጢያቶች ዋጋ ሳንከፍል ማናችንም ከዚህች ምድር አንሄድም። ምንጊዜም እግዚአብሄርን ያለመታዘዝ መንገዶችን ስንመርጥ፥ ያ የምንመርጠው መንገድ ዋጋ እንደሚያስከፍለን እያወቅን ቢሆን ምናልባት መንገዳችንን እንድናስተካክል ይረዳን ይሆናል። ምናልባት ከብዙ ዋጋ መክፈሎች ያድነን ይሆናል። ምናልባት የእግዚአብሄርን ምህረት እንደ ፈቃድ በመጠቀም ከምንገባባቸው ትልልቅ ስህተቶች ያድነን ይሆናል።   “Our true success in this life is being able to fulfill the purpose we were created for!” Icon-facebook Youtube Instagram for the Kingdom through Christ ! Scroll to

Scroll to Top