ብልጫ

ዛሬ አንድ ነገር አስብ ነበር። በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያሉ መንታ ወንድማማቾች ያእቆብና ኤሳው። በ27ተኛው ምእራፍ ላይ ነው ይስሐቅ ሸምግሎ አይኖቹ ለማየት በፈዘዙ ጊዜ፥ ታላቁን ልጁን ኤሳውን ጠርቶ “ልጄ ሆይ እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም። አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፤ ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።” በማለት ኤሳውን የሚጠይቀው። ኤሳው ታዲያ አባቱ ባለው መሰረት አደን ሊያድን ወደ ምድረበዳ ይሄዳል። ይሄን ጊዜ ነው እንግዲህ መረጃውን ከእናቱ በመስማት እና በእናቱ በመታገዝ ታናሽ ወንድሙ ያእቆብ በአቋራጭ ገብቶ የኤሳውን በረከት በሙሉ የወሰደው። በረከቱ እኮ ተስፋ የተገባው ለኤሳው ነበር። ይስሐቅ ሊባርክ የወደደውና በረከቱን በሙሉ መስጠት የፈለገው ለኤሳው ነበር። ያእቆብ ግን ፈጣን ነው፥ አባቱ የሚወደውን ነገር ይዞ ለመቅረብ ፈጣን ነው። የሚውለው እራሱ እዚያው አባቱ ያለበት ሰፈር፥ በረከት ያለበት አካባቢ ነው። እኔ ሳስበው እንደ ያእቆብ የበረከት ትርጉም የገባው ሰው ያለ አይመስለኝም። በኋላ ላይ እኮ ታሪኩን ስታነቡት፥ ስለ በረከት ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎ አሸነፈ የተባለለት አስገራሚ ሰው ነው። ያእቆብ ስለ በረከት ከወንድሙ ጋር ታግሏል፣ ከአጎቱ ከላባ ጋር ታግሏል፣ ከዚህም አልፎ ከእግዚአብሔርም ጋር ታግሏል። ከአብርሀም ጀምሮ እግዚአብሔር ሲገባላቸው የኖረው የተስፋ ቃል በደምብ እንደገባው አልጠራጠርም። የአብርሀም በረከትም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ እንዳለፈ ስለሚያውቅ ይመስለኛል በምስር ወጥና በእንጀራ አታሎ ከታላቅ ወንድሙ ከኤሳው ብኩርናውን የተቀበለው። አይገርምም? በረከት እኮ የታዘዘው ለታላቁ ነበር። ይስሀቅም የፈለገው ኤሳውን መባረክ ነበር። ያእቆብ ግን ፈጣን ነው፥ ውሎው ደግሞ እዚያው አባቱ ያለበት አካባቢ ነው። ውሎው የአባቱን ድምጽ ከሚሰማበት፣ የአባቱን ጠረን ከሚያሸትበት የራቀ አልነበረም። አባቱ የፈለገውን ነገር ለማወቅ እዚያው ቅርብ ነው፥ ብዙ አይርቅም። እዚያው የአባቱን ፍላጎት ቶሎ የሚሰማበት እና የሚያውቅበት ሰፈር ነው የሚውለው። እኛ ግን የት ነው የምንውለው? ውሎአችን የት ነው? የት ሰፈር ነው የምንውለው? መቼም ስለ geographical location አይደለም እያወራን ያለነው። ልባችን የት ሰፈር ነው የሚውለው? ጆሮአችን የት ነው ያለው? ቅርብ ነን? እዚያው እግዚአብሔር የሚገኝበት ሰፈር ነን ያለነው? ሲናገር ቶሎ የምንሰማበት፣ ፍላጎቱን የምናውቅበት ሰፈር ነን ያለነው? በረከት ያለበት ሰፈር ነው የምንውለው? ወይንስ እንደ ኤሳው ሩቅ ሰፈር ነው የምንውለው? እዚያው ድምጹ ሰፈር ነው ጆሮአችን ያለው? ወይንስ ሌላ ቦታ ነው ያለው? ምንድነው ቀኑን ሙሉ ስንሰማ የምንውለው? እንደ ኤሳው እኮ ብዙ የተስፋ ቃል ሊኖረን ይችላል። እግዚአብሔር እኮ ሊባርከን ፈልጎ ሊሆን ይችላል። እንደ ኤሳው እኮ አባቴ ይባርከኛል ብለን ተስፋ እያረግን ይሆናል ያለነው:: ዋናው ጥያቄ ግን የት ነው የምንውለው?  እዚያው ከተስፋ ሰጪው ሰፈር ነው የምንውለው? እግዚአብሔር ሲናገረን የምናዳምጥበት ቦታ ነው ያለነው? እግዚአብሔር ሲፈልገን የምንገኝበት ስፍራ ነው ያለነው? 

በመዝሙር 89 ላይ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲናገር እንዲህ አለ። “ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት። እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች። ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም። ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ። እውነቴና ምሕረቴም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል። “አያችሁ እግዚአብሔር ምን አለ? ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት አለ። ዳዊት እግዚአብሔር ሲመጣ ያገኘው ሰው ነበር። ዳዊት ራሱን ለእግዚአብሔር ያስገኘ ሰው ነበር። ዳዊት ውሎው ልክ እንደ ያእቆብ እዚያው አባቱ ባለበት ሰፈር ነበር፥ ቅርብ ነበር። ውሎው በጎች እየጠበቀ ስራ ተሰጥቶት ምድረበዳ ላይ ሆኖ፥ ስራ ላይ ሆኖ እራሱ ዳዊት ዝማሬ ውስጥ ነው። አምልኮ ውስጥ ነው። የእግዚአብሔር ህግና ስርዓት ውስጥ ነው። ስራ ስለተሰጠው ቢዚ ነኝ፥ ስራ ላይ ነኝ ሳይል ልቡ እግዚአብሔርን ፍለጋ ላይ ነበር። ዳዊት በእግዚአብሔር የተቀባው እራሱን/ልቡን በእግዚአብሔር ሊገኝ የሚችልበት ስፍራ ላይ ስላስገኘ ነው። እግዚአብሔር ምን አለ? ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱሱንም ቅባት ቀባሁት አለ። የሆነ location አለ እግዚአብሔር እኛን ማግኘት የሚፈልግበት፣ ቅባቱ የሚፈስበት፣ የእግዚአብሔር ህልውና የሚፈስበት መንፈሳዊ ስፍራ አለ። ይሄ ቦታ አደባባይ ላይ አይደለም። ግርግር ውስጥ አይደለም። ሶሻል ሚዲያዎቻችን ውስጥም አይደለም። እግዚአብሔር እኛን ማግኘት የሚፈልግበት ልዩ የሆነ ቦታ አለ። የእኛ ስራ ቅባቱ ስር መቀመጥ ብቻ ነው። ቅዱስ ቅባቱ ከሚፈስበት ስር ራሳችንን ማስቀመጥ ብቻ ነው። ይሄንን ለማድረግ ታዲያ ውሳኔ እና ቆራጥነት ያስፈልጋል። መዝጋትም ካስፈለገ ብዙ መዝጋት ያለብን ሚዲያዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙ መተው ያለብን የማይጠቅሙን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እራሳችን እናውቃቸዋለን ሰው ይሄንን ይሄንን ማለት አያስፈልገንም። ይሄንን ማድረግ ከከበደን እና ጸጋ ካስፈልገን ደግሞ፥ እንጠይቀው እንጂ እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ የምንለምነውን ሁሉ የሚያደርግ እና በብዙ የሚረዳን መልካም አምላክ ነው። እኛ ፈቃዳችንን ሰጥተን እንለምነው እንጂ፥ ሀይል የእርሱ ነው፥ ማስቻል የእርሱ ነው፥ መንፈስ ቅዱስ እኮ የተሰጠን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ሕይወት እንኖር ዘንድ ድካማችንን ሊያግዝ ነው። 

በረከቱ ለኤሳው ቢታዘዝም ያእቆብ በመገኘት በለጠ። በፍጥነት፣ የአባቱን ፍላጎት ለማድረግ ከእናቱ ጋር በመተባበር እና ቶሎ በማድረግ በልጦ ተገኘ። እራሱን በአባቱ ፍላጎት ውስጥ አስገኘ። አንዳንድ ጊዜ ወገኖቼ ብዙዎቻችን እግዚአብሔር ተስፋ ገብቶልኛል እንላለን። እውነት ነው እግዚአብሔር የተስፋ አምላክ ነው ብዙ ተስፋዎችንም ሰጥቶናል ነገር ግን ከእኛ የሚጠበቀውን እያደረግን ነው ወይ? ሌላው ቀርቶ እግዚአብሔር እንደተናገረው ሊባርከን ሲመጣ እና ልክ ይስሀቅ ልጁን ሊባርክ ፈልጎ አምጣልኝ ብሎ የሚፈልገውን እንደነገረው የበረከቱን መንገድ ሊያሳየን እና ሊናገረን ሲመጣ እኮ እኛ በቦታችን የለንም። ልባችን ሌላ ሌላ ቦታ ላይ ነው። ሀሳባችን በብዙ ሌሎች ጊዜያዊ እና ምንም ጥቅም በሌላቸው ተራ ነገሮች የተከፋፈለ ነው። የእግዚአብሔር ተስፋ እኮ የእኛን መገኘት፣ የእኛን መታዘዝ እና የእኛን ከእርሱ ጋር መራመድ የሚጠይቅ ነው። ብዙ እንጸልያለን ልንል እንችላለን፥ ግን ውሎአችን የት ነው? ወገኖቼ ጸልየን ጨርሰን ዝም ብለን በማይጠቅሙን ወሬዎች ውስጣችንን ስንሞላ ከዋልን፥ ጸሎታችን ብቻውን የትም አያደርሰንም። የተጠራነው የሕይወት ለውጥ እንድናደርግ ነው። ወደ ክርስቶስ እንድናድግ ነው፥ ወደፊት እንድንራመድ ነው። የተጠራነው እኮ ከእርሱ ጋር ለመኖር ነው።  መዝሙረኛው እኮ ቆይቼ የእግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት እንዳለው ይቻላል እኮ ሌላ ሌላውን ትቶ ከእግዚአብሔር ጋር መዋል ይቻላል። ቢዚ ሆነን እራሱ ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ይቻላል። እየነዳን ከእግዚአብሔር ጋር ማውራት ይቻላል፣ cook እያረግን ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ይቻላል፣ ስራ ቦታችን ሆነን እየሰራን ልባችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ይቻላል። እግዚአብሔርን ለማሰብና ለመፈለግ የሚከለክለን ምንም አይነት ህግም ቢዚነትም የለም። ምነው ምንስ ቢዚ ብንሆን ለሶሻል ሚዲያዎቻችን እና ለተለያዩ ምንም ለማይጠቅሙን ኢንፎርሜሽኖች ጊዜ አለን አይደል እንዴ? እንዲያውም የቢዚነታችን አንዱ ተባባሪ አካል ይሄ አይደለም እንዴ? ልባችንን የገዛው፣ ሀሳባችንን የማረከው፣ ፍቅራችንን የወሰደው የዘመኑ ጣኦት ይሄ አይደለም እንዴ? አሁን ላይ እኮ ኢንፎርሜሽን ሳንሰማ ከዋልን፣ ስለ ሰዎች ታሪክ ሚዲያ ላይ ሳንሰማ ከዋልን፥ የሆነ ነገር ከፍተን ሳንሰማ ከዋልን እኮ ምድር መሽከርከሯን የምታቆም ነው የሚመስለን። እስኪ እንጹም አሁን በዚህ ዘመን እኮ የምግብ ጾም ከሶሻም ሚዲያ እና ከሌሎች ነገሮች ጾም ይልቅ ቀላል ሆኗል። 

ብዙ ኢንፎንሜሽን እያመለጠን ነው። ያምልጠና። በማይጠቅመን ዜናዎች መቅረት የቱ ጋር ነው ሕይወታችን የተጎዳው? መንፈሳዊ አለም ላይ የሚያመልጠንስ በረከት? አንዳንድ ጊዜ እኮ አበላልጠን የቱ እንደሚበልጥ አስበን መምረጥ የምንገደድባቸው እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች አሉ። አንዳንድ ጊዜማ ከነመፈጠራችን እኛን የማያውቁንን ሰዎች ታሪክና ፎቶግራፍ ስንከታተል እኮ ነው ክቡር ጊዜያችንን የምናጠፋው። ስንሰማ የምንውለው ነገር ሁሉ ምድራዊ ነገር ብቻ ሆኖ፥ ስጋዊ ክርስቲያኖች እያደረገን ነው። ስንሰማ ከምንውላቸው ነገሮች እየተወሰድን፥ ከአለማውያኖች ጋር በብዙ ነገር አንድ እየሆንን ነው። በሀሳብ፣ በንግግር፣ በድርጊት እየተመሳሰልን ነው። እስኪ አስቡት ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር የሚውል ሰው የመንፈስ ፍሬን ያፈራል። ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ በጎነትን፣ ቸርነትን፣ የዋህነትን፣ እግዚአብሔርን መፍራትን ያፈራል። ሌላ ሌላ ስጋዊ ነገር ሲሰማ የሚውል ደግሞ የሚያፈራው የስጋን ስራ ብቻ ነው። ስንሰማና ስናይ በምንውላቸው ነገሮች መንፈሳችንን ሳይሆን ስጋችንን ነው ስንመግብ የምንውለው። በጀመርነው መንፈሳዊ ጉዞ ላይ መንፈስና ስጋችን በሚቀዋወሙበት እና በሚታገሉበት በዚህ መንፈሳዊ ትግል ውስጥ የሚያሸንፈው እኛ የመገብነው ነው። መንፈሳችንን ስንመግብ ከዋልን መንፈሳችን ያሸንፋል። ስጋችንን ስንመግብ ከዋልን ደግሞ ስጋችን ያሸንፋል። ከእግዚአብሔር ሀሳብ የሚያጎለንን ስጋችንን ስንመግብ አለመዋላችንን እርግጠኞች ብንሆን በጣም መልካም ነው። 

እስኪ እንሞክረው፥ ስልካችን ላይ ያሉትን ጊዜ ገዳይ ሚዲያዎች ምንም አይጠቅሙንም ብለን የምናስባቸውን ሚዲያዎች እስኪ እንዝጋ። የdistruction በሮችን እስኪ እንዝጋ። አንዳንዴ እኮ መጨከን መልካም ነው። ሕይወታችንን ያተርፍልናል። አባቶቻችን እኮ በብዙ መጋደል እና ዋጋ መክፈል ነው ለእግዚአብሔር ኖረው ያለፉት፥ በነፍሳቸው ተወራርደው እኮ ነው የኖሩት። እግዚአብሔር ጋር ለመድረስ እኮ ዋጋ ይከፈላል። ለትንሽ ጊዜ እስክንለምደው ይደብረን ይሆናል ይደብረና ምን ችግር አለው? እግዚአብሔርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ ተብለን በታዘዝነው መሰረት ራሳችንን ከምናስለምድባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ እኮ ይሄ ነው። የውሳኔ ሰዎች እንሁን፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ጨካኞች እንሁን። ምናለበት ለመልካም ነገር ጨካኞች ብንሆን፥ ነፍሳችንን ለማትረፍ፣ ጊዜያችንን ከጠላት ለመናጠቅ፣ ህይወት ወደሚገኝበት ስፍራ ልባችንን ለማድረግ ብንጨክን ምን አለበት? ለጨዋታ የሚሆን ብዙ ትርፍ ጊዜ እኮ የለንም። በዚህች ምድር ላይ የተሰጠን ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ብቻ የሚበቃ ነው። ለሌላ እርባና ለሌለው ትርፍ ጨዋታ የሚሆን ጊዜ የለንም። አንዳንዶቻችን እኮ ብዙ ጊዜ እራሱ አልቀረንም እዚህች ምድር ላይ ግን አሁንም ጨዋታ ላይ ያለን ነው የምንመስለው። ጠላት ህይወታችን ላይ ትልቅ እድል ያገኘው፥ እኛን በሚማርከን በዚህ አለም ሲስተም ጠላልፎ በመጣል እና ክቡር ጊዜያችንን በማቃጠል ነው። 

ሶሻል ሚዲያ መጠቀም ሀጢያት ነው እንዴ? እስኪ ሀጢያት ነው ወይንስ ሀጢያት አይደለም ከሚለው ጥያቄ ከፍ ብለን፥ ለጀመርኩት መንፈሳዊ ጉዞ ይጠቅማል ወይንስ አይጠቅምም ወደሚለው ጥያቄ እንግባ። ለእግዚአብሔር ክብርን ያመጣል ወይንስ አያመጣም ወደሚለው ሀሳብ እንደግ። ሌላው ቀርቶ በዚህ ዘመን ሚዲያው ላይ መንፈሳዊ ቻናሎች ተብለው እራሱ የተቀመጡትን እየለየን ነው መስማት ያለብን። ባለፈው ዮትዩብ ስከፍት፥ ዘማሪ እገሌ እና ዘማሪ እገሌ በአንድ መድረክ ላይ ተገናኙ ይላል የቪዲዮው ርእስ። ያው የርእሱ አላማ ሰዎች ዘማሪ እገሌና እገሌ ሲገናኙ ለማየት ቪዲዮውን እንዲከፍቱት ነው። ቆም ብዬ ሳስበው ግን አሁን ዘማሪ እገሌና እገሌ አንድ መድረክ ላይ መገናኘታቸውን በማየቴ እንዲያው ሊያዝናናኝ ከቻለ ነው እንጂ፥ የትኛዋ ነፍሴ ናት ወደ እግዚአብሔር የምትቀርበው? ምኔ ነው የሚታነጸው? የትኛው መንፈሳዊ ህይወቴ ነው የሚያድገው? ብዙ ሰው ግን ያያል። እኔ ይሄንን ዘመን ሳየው አንድ ነገር አስባለሁ። የተፈጠርነው እኮ ከመንፈሳዊ ረሀብ ጋር ነው። ሰው ስጋዊ need እንዳለው ሁሉ መንፈሳዊ need ም አለው። ውስጣችን የእግዚአብሔር ህልውና ብቻ የሚሞላው ክፍተት እና እርሱ ብቻ እንዲያጠግበው የተሰራ ረሀብ አለ። በጣም የማከብረው የእግዚአብሔር ሰው ዶክተር ማሙሻ ሲናገር ምን አለ፥ ረሀብ እኮ ቆሻሻም ያስበላል አለ። አንዳንዴ ረሃብ እንዳይሆን ብዙ ቦታ የሚያባዝነን እያልኩ አስባለሁ። ትውልዱ እኮ እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ክብር ተርባል ግን ረሀቡን የሚያጠግብበትን ትክክለኛ ቦታ አላገኘውም ወይንም በብዙ ዲስትራክሽኖች እየተሳበ ውስጡ ያለውን መንፈሳዊ ረሀብ ለማስታገስ ይሄንንም ያያል ያንንም ይሰማል። እውነተኛ ጥጋብ እና እርካታ ያለው ግን እኛ እና እግዚአብሔር በምንገናኝበት መንፈሳዊ ስፍራ ላይ ነው። መንፈሳዊ እድገት ያለው እየመረጥን እና እያስተዋልን በምንጠቀምባቸው ትክክለኛ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ምግብ በሚመግቡ፥ እውነትን ሳይሸቃቅጡ የእግዚአብሔርን ቃል በቅንነት በምንማርባቸው ትምህርቶች ውስጥ ነው። 

ብዙ ምርኮ መበዝበዝ የምንችልበትን መንፈሳዊ አቅም ይዘን ተቀምጠን፥ እኛ እራሳችን ነፍሳችን በየቀኑ ተበዝብዛ እያለቀች ነው። እንደ ያእቆብ እዚያው ቅርብ ሰፈር መዋል እየቻልን፥ ልክ እንደ ኤሳው ሩቅ ሰፈር እግዚአብሔር የሌለበት ምድረበዳ ላይ እየዋልን ነፍሳችን በጥም እየደረቀች፥ በረከታችን ደግሞ በጠላቶች እየተበዘበዘ ነው። ውድ ጊዜያችን እየተበላ ነው፥ ጠላት እያሳሳቀ ማየት የምንፈልጋቸውን ፍላጎቶቻችንን እያጠና እና የትም ሳንሄድ እዚያው እጃችን ላይ ማየት እና መስማት የምንፈልጋቸውን ነገሮች እያመጣ ከብዙ በረከት እና ሕይወት እያጎደለን ነው። ወገኖቼ እባካችሁ እንንቃ እናስተውል። አንዳንዴ እምቢ ማለትን መጨከንን እንማር። ለእግዚአብሔር ክብር፥ ለራሳችንም ጥቅም ዋጋ መክፈልን እንማር። ሁሉ ተፈቅዶልን ቢሆንም፥ ሁሉ እኮ የሚጠቅመን አይደለም፥ ሁሉ እኮ የእኛ አይደለም። እምቢ የምንላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እንደ እግዚአብሔር ሀሳብ ዘመኑን እየዋጀን ስንኖር፥ ይለፈኝ የምንላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የስጋችን ፍላጎት እና ምኞት በልጦብን ልክ እንደ ኤሳው ብኩርናችንን አናቃልል። የእግዚአብሔርን ነገር አናቃልል። አንዳንድን በረከቶች አንዴ ካቃለልናቸው በኋላ፥ ሌላ ጊዜ ስንባንን እና በእምባ ስንፈልጋቸው  የማናገኛቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ዘመናችን ከተወሰደ በኋላ፣ ብዙ ጊዜያችን ከተበላብን በኋላ የምንነቃ ሰዎች አንሁን። ብዙ ከሄድን በኋላ፣ ብዙ ካላስተዋልን በኋላ መጨረሻ ላይ የምንቆጭ ሰዎች አንሁን። በተሰጠን ዘመን፥ ተለክቶ በተሰጠን ጊዜ አንቀልድ። ይሄ የሕይወት ጉዳይ ነው። ጠላት ሁልጊዜ እኛን የሚያገኘን ሊማርከን በሚችሉ ነገሮች መሆኑን አንዘንጋ። ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ሕይወት እና ሞት በረከትና መርገም ከፊታችሁ አለ። በረከትን ምረጡ፥ ሕይወትን ምረጡ ብሎ ሕዝቡን እንደመከረ ዛሬም እግዚአብሔር ይመክረናል። ዛሬም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በየቀኑ ሕይወትን ምረጡ፥ በየቀኑ በረከትን ምረጡ ይለናል። 

በመጨረሻ አንድ ነገር በማለት እንጨርስ፥ በዚህ ዘመን ለእግዚአብሔር ልክ እንደ ስጦታ በፊቱ የምናቀርበው እና የምንሰጠው ውድ ስጦታ ትኩረታችንን ነው፥ ሙሉ ትኩረታችንን ነው።  በተለይ በዚህ ዘመን እግዚአብሔርም አስቀድሞ የሚፈልገው፥ ሰይጣንም በየቅዱሳን ቤት ለመግባት ትልቅ እድል ያገኘበት ጉዳይ የገዛ ትኩረታችንን በመውሰድ ነው። ስለዚህ የየቀን አላማችን፥ የገዛ ትኩረታችንን ከብዙ ነገሮች እየነጠቅን ለእግዚአብሔር እንደ መስዋእት በማቅረብ ከእርሱ ጋር መሆን፥ ሕይወትን ከነ ትርፋ መኖር፥ ጸጥታን ኢንጆይ ማድረግ፥ በእግዚአብሔር ህልውና ውስጥ መቆየት፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደግ፣ ውስጣችን ባሉት ስጦታዎች ሁሉ ፍሬያማ እና ትርፋማ በመሆን የተሰጠችንን ይህቺን በጣም አጭር ምድራዊ ቆይታ ለዘላለም እንዳንቆጭባት አርገን ክቡር ጊዜያችንን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መጠቀም ነው። 

“ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውሀ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል” (ምሳሌ 20፡5) 

"Our true success in this life is being able to fulfill the purpose we were created for!"

for the Kingdom through Christ !

©2026, Hana Elias. All Rights Reserved

Scroll to Top