Author name: hanael

Article

መድሀኒት

Home Blog Book About Contact X Order Book መድሀኒት Audio በሀገራችን አንድ የተለመደ አባባል አለ። “በሽታውን ያልተናገረ መድሀኒት አይገኝለትም” ይላሉ። አባባሉ እውነት ነው። አንድ ሰው ሲታመም፥ እንደታመመ መጀመሪያ ቀድሞ የሚረዳው እራሱ ያ ሰው ነው። ይሄ ሰው ታዲያ በሽታውን የመናገርና መፍትሄ የማግኘት፥ ወይንም ደግሞ ዝም በማለት ህመሙን የመደበቅ መብት አለው፥ በተለይ ደግሞ በጣም ካልባሰበትና ከአቅሙ በላይ ካልሆነ። ህመሙን መደበቁ ግን፥ መድሀኒት እንዳይገኝለት አልፎም ደግሞ በሽታው እንዲብስና የበለጠ እንዲጎዳው ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ አንድ የታመመ ሰው፥ መድሀኒት ያገኝ ዘንድ መጀመሪያ እንደታመመና እርዳታ እንደሚያስፈልገው ማመን አለበት ምክኒያቱም፥ የሚሰጠውን መድሀኒት መውሰድና መዳን ወይንም ደግሞ ህመሙን ማስታገስ የሚችለው፥ እንደታመመ ሲያምን ብቻ ነው።  ስለዚህ ጉዳይ ሳስብ፥ ወደ ሀሳቤ የሚመጣ አንድ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል አለ። ክፍሉ የእግዚአብሄር መልአክ መጥቶ ስለ ኢየሱስ መወለድ በሜዳ በጎቻቸውን ሲጠብቁ ላደሩ እረኞች የሚናገርበት ክፍል ነው። መልአኩ በድንገት ለእረኞቹ ተገልጦ እረኞቹን ያላቸው ነገር ይሄ ነው። “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” አላቸው። የመልአኩ አባባል የሚገርም ነው! “አሁን የምነግራችሁ የምስራች፥ ለህዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ ነው” አለ። መቼም አንድ ህጻን ሲወለድ፥ ደስታ የሚሆነው ለወለዱት ቤተሰቦቹና በቅርቡ ላሉት ወዳጅ ዘመዶቹ ብቻ ነው እንጂ፥ ለህዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ ሊሆን አይችልም። እንደ መልአኩ አባባል ከሆነ ግን፥ የዚህ የተወለደው ህጻን ደስታ የቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን የህዝቡ ሁሉ ነው። የህጻኑ መወለድ ለህዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታና የምስራች የሆነበትን ሚስጥር ታዲያ መልአኩ እንዲህ በማለት ይናገራል። የተወለደው ህጻን ለእናንተ የሚሆን መድሀኒት ነው አለ። መቼም ከላይ እንዳልነው፥ ሰው መድሀኒት የሚያስፈልገው ሲታመም ነው። ጤነኛ የሆነ ሰው መድሀኒት አያስፈልገውም።  አምላክ ሲሆን ራሱን ከሰው ልጆች አንዱ ለማድረግ ፈቅዶ ወደ ምድር የመጣው ኢየሱስ፥ የሰው ልጆችን መከራ ሊቀበልና በመስቀል ላይ ሊሞት ያስፈለገው፥ በአዳምና በሄዋን አለመታዘዝ ምክኒያት የሰው ዘር በሙሉ በሀጢያት በሽታ ስለተበከለ ነው። አንድ ሰው መድሀኒት ለመውሰድ መታመሙን አምኖ መቀበል እንደሚያስፈልገው ሁሉ፥ ኢየሱስ ስለ ሀጢያታችን የከፈለውን ዋጋ በመቀበል መዳን የምንችለው፥ መጀመሪያ ከፍጥረታችን ሀጢያተኞች መሆናችንን ስናምን ብቻ ነው። ሀጢያተኞች መሆናችንን በመረዳት፥ መድሀኒት ለመሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የከፈለውን ዋጋ አምነን መቀበላችን፥ እግዚአብሄር የሰው ልጆችን ከሀጢያት በሽታ ለማዳን ያዘጋጀው ብቸኛ መንገድ ነው። በትንቢተ ኢሳይያስ መጽሀፍ ላይ፥ ነቢይ የሆነው ኢሳይያስ በመጽሀፉ 53ተኛ ምእራፍ ላይ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦   “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።”   በማለት ይናገራል። ከላይ እንዳነበብነው ቃል፥ ስለ እኛ መተላለፍ የቆሰለው፣ ስለ እኛ በደል የደቀቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። “እግዚአብሄር የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” እንደሚለው፥ እግዚአብሄር የዓለምን ሁሉ ሀጢያት ሰብስቦ ያኖረው፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብቻ ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ሀጢያታችንን የተሸከመልን ሰውም፣ መልአክም የለም። ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ የእኛን ሀጢያት ዋጋ በመክፈል ከእግዚአብሄር ጋር ሊያስታርቀን የቻለ ሰውም መልአክም የለም። ለዚህ ነው ኢየሱስ በራሱ አንደበት ሲናገር “እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ፥ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት በዮሀንስ ወንጌል 14፡6 ላይ የተናገረው። ወደ አብ የመድረሻ መንገዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ከእግዚአብሄር ጋር የመታረቂያ መንገዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። የዘላለምን ህይወት የማግኛ መንገዱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሌላ መንገድ የለም። ሌላ አማራጭ መንገድ የለም። ሌሎች አማራጭ መንገዶች ቢኖሩ ኖሮ፥ ሌላ ከሀጢያት በማዳን እኛን ከእግዚአብሄር ጋር የሚያስታርቁን መንገዶች ቢኖሩ ኖሮ፥ ለምሳሌ መላእክቶች እኛን ከእግዚአብሄር ጋር ማስታረቅ ቢችሉ ኖሮ፥ የሀይማኖት አባቶች ሀጢያታችንን በመሸከም እኛን ከእግዚአብሄር ጋር ማስታረቅ ቢችሉ ኖሮ፥ ወይንም እኛ በምንሰራቸው ጥሩ ጥሩ ስራዎች መዳን ብንችል ኖሮ፥ ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ይሄንን ሁሉ ዋጋ መክፈል ለምን ያስፈልገው ነበር? ኢየሱስ ለምን የአምላክነት ክብሩን ትቶ ሰው ሆነ? ለምንስ ወደ ምድር መጥቶ ሀጢያታችንን ተሸከመ? ለምን የሀጢያታችንን ዋጋ ከፈለ? ከሀጢያት የመዳኛ መንገዱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ስለሆነ ነው። ከእግዚአብሄር ጋር የመታረቂያ መንገዱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ስለሆነ ነው። ከሞት በኋላ ያለውን የዘላለምን ህይወት የማግኛ መንገዱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ስለሆነ ነው። ከዚህ ውጪ እኛ የምንድንበት ሌላ መንገድ ስለሌለ ነው። ወደ አንድ ቤት ውስጥ ለመግባት የቤቱን በር ማግኘት እንዳለብን ሁሉ፥ ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት በሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን፥ ኢየሱስ እራሱ በዮሀንስ ወንጌል ምእራፍ 10 ላይ በራሱ አንደበት  ይናገራል።  መዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሀጢያታችን የከፈለውን ዋጋ በማመን ብቻ ነው። መዳን በስራ አይደለም በእምነት ብቻ ነው። ለመዳን የእኛ ስራ አያስፈልግም። እኛን ከሀጢያት ለማዳን ክርስቶስ ከሰራው ስራ ጋር አብሮ የሚደመር የእኛ ስራ የለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የከፈለው ዋጋ እኛን ለማዳን በቂ ሆኖ በእግዚአብሄር ፊት ተቀባይነትን አግኝቷል። የሀጢያት ዋጋው በክርስቶስ ተከፍሏል። መልካም ነገሮችን የምናደርገው ለመዳን አይደለም። መልካም ነገሮችን የምናደርገው፥ በክርስቶስ አምነን ስለዳንን ነው። ለመዳን አንሰራም፥ ስለዳንን ግን እንሰራለን። በክርስቶስ አምነን ከዳንንና ወደ እግዚአብሄር መንግስት ከገባን በኋላ በምናደርጋቸው መልካም ተግባሮች ደግሞ እግዚአብሄር ይደሰታል። በሰማይ ቤትም ዋጋን ይሰጠናል። የዳነው ግን በስራ አይደለም በእምነት እንጂ። መጽሀፍ ቅዱስ በዮሀንስ ወንጌል ምእራፍ 3 ቁጥር 16 ላይ ሲናገር እንደዚህ ይላል።  “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” ይላል። መዳን በእምነት ብቻ እንደሆነ ከተረዳን በኋላ፥ በክርስቶስ ማመን ማለት ታዲያ ምን ማለት ነው ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የሰውን ልጅ ከእግዚአብሄር የለየው፥ በአዳምና በሄዋን አለመታዘዝ ምክኒያት ወደ ሰው ዘር ሁሉ የገባው ሀጢያት ነው። “ይሄንን ፍሬ በበላችሁ ጊዜ ሞትን ትሞታላችሁ” ብሎ አስቀድሞ እግዚአብሄር ለአዳም እንደተናገረው፥ ፍሬውን በበሉ ጊዜ ሞተዋል። ከእግዚአብሄር ህይወት ተለይተዋል። ሞት ማለት ከእግዚአብሄር መለየት ማለት ነው። ህይወት የተፈጠረው በእርሱ ስለሆነ፥ ከእርሱ የተለየ ህይወት በሙሉ የሞተ ነው። አንድ ሰው ከእግዚአብሄር ከተለየ፥ የሚኖረው እዚህ ምድር ላይ ብቻ ነው እንጂ ያለው በዘላለም ሞት ውስጥ ነው። በዚህች ምድር ያለው ቆይታ ሲያበቃ፥ የሚሄደው ወደ ዘላለም ሞት ወይንም ወደ ገሀነመ እሳት ነው።  ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ታዲያ የዚህን ሀጢያት ዋጋ በመክፈል እና የዘላለምን ሞት ከሰው ልጆች ላይ በማስወገድ፥ በእግዚአብሄርና በሰው ልጆች መካከል ተቋርጦ የነበረውን ህብረት ለማስተካከል ነው። በሀጢያት ምክኒያት ለሞተው መንፈሳችን ህይወትን በመስጠት፥ እንደገና ህያዋን እንድንሆንና የዘላለምን ህይወት ወይንም መንግስተ ሰማያትን እንድንወርስ ነው። ይሄንን የዘላለም ህይወት የሚወርሱት ታዲያ፥ መጀመሪያ በሰው ዘር ሁሉ ላይ በመጣው ሀጢያት ምክኒያት ሀጢያተኞች መሆናቸውን የሚያምኑ እና ስለዚህ ሀጢያት ክርስቶስ የከፈለውን ዋጋ አምነው የሚቀበሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። ኢየሱስ ለዓለም ሁሉ ቢሞትም፥ የሚድኑት ግን በእምነት የሚቀበሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። መጽሀፍ ቅዱስ በዮሀንስ ወንጌል ምእራፍ 3 ቁጥር 36 ላይ እንዲህ ይላል። “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” ይላል።  ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ሳይመጣ በብሉይ ኪዳን የነበረውን ስርዓት ስትመለከቱ፥ ሰዎች ሀጢያትን ሲሰሩ የእንስሳቶችን ደም በማፍሰስ ጊዜያዊ የሆነ የሀጢያት ስርየትን ያገኙ ነበር። ታዲያ ሀጢያታቸውን ይዞ በእግዚአብሄር ፊት የሚቆመው ካህን፥ እርሱም ሰው

Article

መውደድ

Home Blog Book About Contact X Order Book መውደድ Audio በልጅነቱ እንደ እኔ ጨዋታ የሚወድ ሰው ያለ እስከማይመስለኝ ድረስ መጫወት በጣም ነበር የምወደው። ገና ከትምህርት ቤት ስንወጣ ልቤ የሚቸኩለው፥ ቶሎ ብዬ ቤት በመሄድ ልብሴን ቀይሬ ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር አባሮሽ እስክንጫወትና ሩጫ እስክንወዳደር ነበር። ታዲያ ገና እኔና እህቴ ከትምህርት ቤት እንደገባን፥ እናታችን ከስራ ትመጣና ለእኔና ለእህቴ መስራት ያለብንን የቤት ስራ አከፋፍላን መሄድ ወዳለባት የማህበራዊ ህይወት ጉዳዮች ትሄዳለች። አብዛኛውን ጊዜ የእህቴ ስራ እቃ ማጠብ ሲሆን፥ የእኔ ስራ ደግሞ ቤቱን ማጽዳት ነው። “በቃ ቶሎ ቶሎ ሰርቼው ሄጄ ልጫወት” እልና ገና ቤቱን መጥረግ እንደጀመርኩ፥ የሰፈር ጓደኞቼ በአጥሩ በኩል ስሜን እየጠሩ ጊቢውን ይደባልቁታል። ድሮም ለመጫወት የቸኮለው ልቤ “በቃ ትንሽ ልጫወትና ቶሎ ተመልሼ እጨርሰዋለሁ” በማለት፥ ጓደኞቼን ለማግኘት ወደ ውጪ እሮጣለሁ። ከጓደኞቼ ጋር ስንሮጥ፣ ስንስቅ፣ ስንቀልድና ስንጫወት ቆይተን ቆይተን ልክ ቀኑ እየመሸ ሲመጣ፥ እናቴና የሰፈር ጎረቤቶቿ ነጭ ነጠላቸውን አንደለበሱ ሰፈር ውስጥ ከነበረ ለቅሶ ቤት ሲመለሱ ከሩቅ አያቸዋለሁ። “ወይኔ ስራዬን ሳልጨርስ እናቴ እየመጣች ነው” ብዬ በሩጫ ወደ ቤት በመመለስ የጀመርኩትን ቤት ጠርጌ ሳልጨርስ ውዷ እናቴ ትገባለች። “ቀጥ ብለሽ መኝታ ቤት ሄደሽ ጠብቂኝ” ማለት በእኛ ቤት አማርኛ፥ መኝታ ቤት ቁጭ ብለሽ እየመጣ ያለውን ዱላ ጠብቂ ማለት ነው። ዱላው ደግሞ እዛው መኝታ ቤት አልጋ ስር ስለሚቀመጥ፥ አንዳንድ ጊዜ ሰባብሬ ብጥለው እራሱ ደስ ይለኛል። በ4 አመት ከእኔ ታናሽ የሆነችው እህቴ ደግሞ በጣም በሚገርም ሁኔታ እንደ እኔ ጨዋታ የማያታልላትና የተሰጣትን ስራ ሳትሰራ የትም ቦታ ለመጫወት የማትሄድ ልጅ ነበረች። ኸረ አንዳንዴ እንዲያውም ስራውን እየሰራች ሳትጫወት ቀኑ ሊመሽባት ይችላል። አሁን ላይ ስለ ልጅነታችን ስናወራ ታዲያ፥ እህቴ የጨዋታ ጊዜዋን በአግባቡ ስላልተጠቀመችበትና መጫወት ባለባት ጊዜ ስላልተጫወተች ሲቆጫት እመለከታለሁ። “እንዴት ነው ታዲያ ጨዋታ ሊያታልልሽ በሚችልበት እድሜ ላይ ሆነሽ ስራን ልታስቀድሚ የቻልሽው?” ብዬ ስጠይቃት፥ የሰጠችኝ መልስ ይሄ ነው። “የተሰጠኝን ስራ ካልሰራሁ እናቴ የምትወደኝ አይመስለኝም። የምሰራው እናታችን በጣም እንድትወደኝ ብዬ ነው” በማለት መልሳልኛለች። እናታችን አሁን ላይ ሆነን የምናነሳውን ይሄንን ትዝታ ስትሰማ “ድሮ ልጅ እያላችሁ የተሰጣችሁን ስራ ያልሰራችሁ ቀናቶችም እኮ እወዳችሁ ነበር።” ስትለን “ታዲያ ለምን የዛኔ አልነገርሽንም ነበር” በማለት ምላሽ እንሰጣታለን። የእህቴን ምላሽና እኔ የተሰጠኝን ስራ ባልሰራሁባቸው ቀናቶች ይሰማኝ የነበረውን ያለመወደድ ስሜት እያሰብኩ ጥቂት ቆየሁ። ስሜቱ በጣም ያስጠላል። ያለመወደድ ስሜት በጣም ከባድ ነው። ይሄ ስሜት ከልጅነታችንም ስላደገብኝ፥ ወደ እግዚአብሄር አባትነት ስመጣ በተለያዩ ቀናቶች ተመሳሳይ ስሜት ሲሰማኝ እራሴን አገኘዋለሁ። አንዳንድ ቀን እግዚአብሄር የሚወደኝ ስለታዘዝኩትና ስላገለገልኩት መስሎ የሚሰማኝ ቀናቶች አሉ። እራሴን ታዲያ ባለመታዘዝ ውስጥ ያገኘሁት ቀን፥ ለእኔ ያለው ፍቅር የሚቀንስ እየመሰለኝ ውስጤ ይረበሻል። ነፍሴ እግዚአብሄር ከሰው ፍጹም የተለየ አስተሳሰብ እንዳለው እስኪገባትና እስክትረዳ ድረስ፥ ዘላለማዊ የሆነውንና ያለ ምንም ምክኒያት ስለወደደኝ በምንም ምክኒያት ሊጠላኝ የማይችል አምላክ እንደሆነ እስክረዳው ድረስ ነው።         በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 15 ላይ፥ ኢየሱስ ስለ ጠፋው ልጅ ምሳሌ እንዲህ በማለት ይናገራል። አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን፦ አባቴ ሆይ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከእነዚህ ሁለት ወንድማማቾች ታናሽ የሆነው ወንድም ታዲያ፥ ከአባቱ የሚደርሰውን ክፍል በመቀበል ወደ ሩቅ አገር እንደሄደና ገንዘቡን አባክኖ እንደጨረሰ፥ ከዚያም በብዙ ረሀብና ችግር ውስጥ ካለፈ በኋላ ወደ ልቡ እንደተመለሰ ይናገራል። ይሄ ልጅ በዚህ ሁሉ መባከንና ማባከን ውስጥ ሲያልፍ በልቡ አልነበረም። በመጨረሻ ግን በምእራፉ ቁጥር 17 ላይ እንደሚናገረው፥ ወደ ልቡ ተመልሶ “እንዴ ቆይ ግን ምግብ የሚተርፋቸው በጣም ብዙ ሰዎች በአባቴ ቤት አሉ አይደል እንዴ? እኔ ታዲያ ለምንድነው እዚህ የአሳማዎችን ምግብ ለመብላት እስከምፈልግ ድረስ በዚህ ከባድ ረሀብ ውስጥ የማልፈው?” ብሎ በማሰብ ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ይወስናል። በጣም የሚገርመው፥ ይሄ ልጅ ቢጠፋም አባቱ ለእርሱ ያለውን ፍቅር ጠንቅቆ የተረዳ ልጅ ነበር። ለዚያ ነው ያለውን ድርሻ አባክኖ ከጨረሰ በኋላ ወደ አባቱ የሚመለስበትን ድፍረት ያገኘው። አብዛኞቻችሁ ታዲያ ታሪኩን እንደምታውቁት፥ የልጁን ወደ እርሱ መመለስ የተመለከተው አባት፥ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ደስታ ውስጥ ገብቶ ባሪያዎቹን እንዲህ በማለት ሲያዛቸው እንመለከታለን። “ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት። ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፥ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላ ደስም ይበለን፥ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ህያው ሆኗል ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም” በማለት ይናገራል። በሌላ ገጽ ደግሞ በቤት ውስጥ ብዙ የሚለፋና የሚደክመው የዚህ የጠፋው ልጅ ታላቅ ወንድም፥ በጣም ብዙ ስለሰራና አባቱን ስላገለገለ ከወንድሙ በተሻለ መልኩ የሚወደድ ይመስለው ነበር። ይሄንንም የሚያስረግጥልን በምእራፉ 29ነኛ ቁጥር ላይ፥ አባት የጠፋውን ልጁን አስመልክቶ ባደረገው የደስታ ዝግጅት ላይ በመናደድ የተናገረው ንግግር ነው። “እነሆ ይህን ያህል አመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሀለሁ፥ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍኩም፥ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጠቦትስ እንኳን አልሰጠሀኝም።” በማለት ለአባቱ ያለውን መገዛትና መታዘዝ ከወንድሙ በተሻለ መልኩ ሊወደድበት የሚገባ ምክኒያት አድርጎ ያስቀምጣል። ይሄ ልጅ መገዛቱ መልካም ነው። የአባቱን ትእዛዝ በትክክል አክብሮ ማገልገሉም እጅግ በጣም መልካም ነው። አንድ የሳተው ትልቅ ነገር ግን ምንድነው? ለአባቱ የሚሰጠው ይሄ ሁሉ አገልግሎት፥ አባቱ እርሱን የወደደባቸው ምክኒያቶች አለመሆናቸውን አለመረዳቱ ነው። አባታቸው እርሱንም ሆነ ወንድሙን የወደዳቸው፥ ስለሰሩና ስላገለገሉት አይደለም። የወደዳቸው ልጆቹ ስለሆኑ ነው። የወደዳቸው ስለወለዳቸው ነው። ሰው ልጁን የሚወደው፥ ስለሰራና ስላገለገለው አይደለም። ሰው ልጁን የሚወደው፥ ስለወለደው ነው።         እኔ ገና ልጅ ባለመውለዴ ስሜቱ በትክክል ባይገባኝም፥ አንድ ወዳጃችን የመጀመሪያ ልጇን ከወለደች በኋላ የነገረችን አንድ ነገር ልቤ ውስጥ ቀርቷል። “ልጄን ወልጄ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያት አለቀስኩ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ተሰምቶኝ የማያውቅ ስሜት ተሰማኝ። ገና ሳያት በጣም ወደድኳት። ድንገት ወደ ህይወቴ መጥታ፥ በህይወቴ ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ በለጠችብኝ። በዚህ መጠን ሰውን መውደድ የምችል እራሱ አይመስለኝም ነበር” እያለች ስትናገር አስታውሳለሁ። እኛ ሰዎች፥ ሌሎች ሰዎችን ስንወድ ሁልጊዜ ምክኒያት አለን። ልጆች ስንወልድ ግን ልጆቻችንን የምንወድበት ምክኒያት የለንም። የምንወዳቸው ስለወለድናቸው ብቻ ነው። ስለወለድነው ብቻ ልጃችንን ዳይፐሩን እየቀየርን፣ እያበላንና እያጠጣን፣ የራሳችንን እንቅልፍና እረፍት እየቀነስን የወለድነውን ልጅ እናሳድጋለን። ይሄንን ሁሉ ዋጋ ስንከፍል፥ ለልጁ ውለታ እያደረግንለት እንደሆነ አይሰማንም፥ ምክኒያቱም ሁሉንም ነገር የምናረገው ውስጣችን ካለው ፍቅር ተነስተን ነው። ለወለድነው ልጅ የሚያስከፍለውን ዋጋ ብቻ ሳይሆን፥ አንዳንዴም ከሚያስከፍለው ዋጋ በላይ ማድረግ ትልቁ ደስታችን ነው። እንዲያውም እነዚህን ነገሮችን ለወለድነው ልጅ አለማድረግ አንችልም። በተለያዩ ከባባድ ምክኒያቶች ይሄንን ለልጆቻችን ማድረግ ባንችል ደግሞ፥ እጅግ በጣም ትልቁ ሀዘናችን ነው። ይሄ የጠፋው ልጅ ወንድም፥ አባታቸው ስለሰሩለትና ስላገለገሉት ሳይሆን ልጁቹ ስለሆኑ ብቻ፥ ከእርሱ ስለተወለዱ ብቻ እንደሚወዳቸው ቢረዳና ቢገባው ኖሮ፥ የወንድሙን መመለስ አስመልክቶ እየሆነ ባለው ደስታ ላይ ተባባሪ ይሆን ነበር። ሌላው፥ ይሄ ታላቅ ወንድም አባቱ ለእርሱ ያለውን ከምንም ነገር ጋር ያልተያያዘ ፍቅር ቢረዳ ኖሮ፥ አባቱን የሚያገለግልበት ምክኒያት ይቀየር ነበር። አገልግሎቱ ባይቋረጥም፥ የሚያገለግለውና የሚታዘዘው እንዲወደድ ሳይሆን ስለተወደደ ይሆን ነበር። አገልግሎቱ በአባቱ የሚወደድበት ምክኒያት ሳይሆን፥ በአባቱ ለተወደደበት ፍቅር የሚሰጠው ምላሽ ይሆንለት ነበር። ሁላችንም እግዚአብሄርን ለማገልገል የተጠራን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን፥ በአገልግሎት ቦታችን ላይ ሆነን ማወቅ ያለብን፥ እግዚአብሄር እኛን የሚወደን ስላገለገልነው አለመሆኑን ነው። ይሄንን ደጋግመን ለራሳችን መንገር አለብን። የእግዚአብሄር ፍቅር እኛ ባገልገልነው መጠን ቢሆን ኖሮ፥ ፍቅሩ በጣም ትንሽ ይሆን ነበር። ሌላው ቀርቶ እግዚአብሄር የሚወደን ቃሉን እየጠበቅን በመታዘዝ ስለምንኖር አይደለም። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሄር አስተሳሰቡ እንደ እኛ እንደ ሰው ስለሚመስለን፥ በፊቱ ጥሩ ህይወት ያለን የመሰለን ሰሞን ለእኛ ያለው ፍቅር የጨመረ ይመስለናል። ነገር ግን ባለመታዘዝና በጨለማ ውስጥ ሆነን የስጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን ስንሄድ፣ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ሆነን የስጋችንን ምኞቶች

Article

አምልኮ

Home Blog Book About Contact X Order Book አምልኮ Audio አንድ በጣም የምወዳት ዘማሪ አንድ ጊዜ አንድ ነገር ስትናገር ሰማሁ እና እውነት ነው አልኩ። ምንድነው ያለችው፥ በህብረት አምልኮቻችን ውስጥ የምናደርጋቸው ስርአቶች በሙሉ እኛን የሚጠቅሙን ናቸው። ለምሳሌ ጸሎቱ ለእኛ ነው፣ ቃሉ ለእኛ ነው፣ ምስክርነቱ ለእኛ ነው፣ ማስታወቂያው ለእኛ ነው፥ አምልኮ ብቻ ግን ለእግዚአብሔር ነው። ከምናደርጋቸው ስርአቶች ውስጥ ለእግዚአብሔር የምንሰጥበት፥ እግዚአብሔር ከእኛ የሚቀበልበት ስርአታችን አምልኯአችን ብቻ ነው። ሆኖም ግን ለዚህ ለእግዚአብሔር ለምንሰጥበት እና ክቡር ለሆነው የእግዚአብሔር ስርአት፥ የሚገባውን ቦታ አንሰጠውም። አምልኮ ብዙ ጊዜ፥ ወይ ወደሚቀጥለው ፕሮግራም መሸጋገሪያ፥ ወይ ደግሞ ሰው ወደ ጉባኤው እስኪገባና እስኪሰበሰብ መቆያ ነገር፥ ልማድ ስለሆነ እንዲያው ካላደረግነው ቅር ቅር የሚለን፥ ብዙ ጊዜ ደግሞ በስሜቶች ብቻ የሚነዳ፥ መንፈሳችን ጋር ሳይደርስ ስጋችንን ብቻ የሚያረካ እና በቃ ከምናረጋቸው ስርአቶች ውስጥ አንዱ ሆኖብናል።  የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ ግን፥ አምልኮ ፍጹም የእግዚአብሔር ሀይል የተገለጠበት፥ አባቶቻችን መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር የተገናኙበት እና ህብረት ያረጉበት፥ የእግዚአብሔር ሀይል እና ስልጣን እንዲሁም ችሎታ የተገለጠበት አስደናቂ ነገር ነው። በነ ኤልሳእ ዘመን በገና ደርዳሪው ልክ በገናውን ሲደረድር የእግዚአብሔር እጅ እንደመጣች እና እግዚአብሔር ለእነዚያ ለሶስቱ ነገስታት ደመናም ዝናብም ሳይኖር ባዶ ሸለቆ በውሀ ሲሞላ ያዩበት መንገድ ሆኗል። አምልኮ በእነ ንጉስ ኢዮሳፍጥ ዘመን ደግሞ ምህረቱ ለዘላለም ነው እያሉ በዝማሬ እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፥ ልክ ምስጋናውን እና ዝማሬውን በጀመሩ ጊዜ ድብቅ የሆነውን ጦር እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ አምጥቶ፥ ድልን በድል ላይ እየጨመረ ባለ ብዙ ድል አርጓቸዋል። እነ ጳውሎስ እና ሲላስን ስንመለከት ደግሞ፥ በመንፈቀ ሌሊት እግዚአብሔርን በዜማ ሲያመሰግኑ እና ሲያመልኩ፥ የብረት ሰንሰለት ከእጃቸው ተበጥሶ፥ የነበሩበት ወህኒ ከነ መሰረቱ ተናውጧል። እውነተኛ አምልኮ ሰንሰለቶች የሚበጠሱበት አስደናቂ ነገር ነው። እኛ ከአምላካችን ጋር በመንፈስ የሆነውን ህብረት የምናረግበት፥ እግዚአብሔር ደግሞ ሲሰራ የምናይበት ነው። እግዚአብሔርን በትክክል ስናመልከው፥ ልክ እንደ ጳውሎስ እና ሲላስ መንፈሳዊ የሆኑ ስውር እስራቶች እና ሰንሰለቶች መበጣጠስ ይጀምራሉ፥ ቀንበሮች መሰበር ይጀምራሉ። የተለያዩ መልሶችን ከእግዚአብሔር እንቀበላለን፥ ልዩ ልዩ መገለጦች ጋር እንደርሳለን። መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ የሆነውን ህብረት ማድረግ እንጀምራለን።  እነዚህን በአምልኮ ውስጥ ያሉትን በረከቶች ተካፋይ የምንሆነው ግን፥ እግዚአብሔር “አምልኮን እቀበላለሁ” ባለበት በራሱ ባስቀመጠልን መንገድ ስናመልከው ብቻ ነው። በህብረቶቻችን ውስጥ ባሉት የዝማሬ ጊዜያቶች ውስጥ፥ ሁለት አይነት የአምልኮ አይነቶች አሉ። አንደኛው በስጋ የሆነ አምልኮ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንፈስ የሆነ አምልኮ ነው። ሰው በመንፈስ ሳይሆን ሊዘምር ይችላል። ሰው በመንፈስ ሳይሆን ሊያጨበጭብ ይችላል፣ እልል ሊል ይችላል፣ ሊዘል ይችላል፣ ሊጮህ ይችላል፥ ብዙ ነገሮችን ሊያደርግ እና ሊሆን ይችላል። ያ ግን እውነተኛ አምልኮ አይደለም። እውነተኛ የሆነ እና ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮ፥ በሁለት ነገሮች ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባው የእግዚአብሔር ቃል በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 4፡24 ላይ በግልጽ ይናገራል። ቃሉ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስ እና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ይላል። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ ስለዚህ የሚሰገድለት በመንፈስ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ ስለዚህ የምንሰዋለትን መስዋእት የሚቀበለው በመንፈስ ሆነን ስንሰዋለት ነው። በስጋ የሆነ አምልኮ እና በመንፈስ የሆነ አምልኮ በጣም የተለያየ ነው። በስጋ የሆነ ስግደት እና በመንፈስ የሆነ ስግደት በጣም የተለያየ ነው። ሰው በመንፈስ ሳይሆን በስጋው ሊሰግድ ይችላል። በመንፈስ የሆነ ስግደት ግን የስጋ ጉልበታችንን ብቻ ሳይሆን፥ መንፈሳችንን እና ነፍሳችንን እንዲሁም መላው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር አምላክነት እያስገዛን ሁለንተናችንን በፊቱ የምናዋርድበት ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ፥ የሚቀበለው በመንፈስ የሆነን አምልኮ እና መስዋእት ነው። ስለዚህ ሁልጊዜም ቢሆን በቤተክርስቲያን፣ በህብረት እንዲሁም በግል አምልኮቻችን ውስጥ ለማምለክ ስንዘጋጅ፥ በመንፈስ ለመሆን መዘጋጀታችን በጣም አስፈላጊ ነው።  በመንፈስ የሆነ አምልኮ ተቃራኒው በስጋ የሆነው አምልኮ ነው። በመንፈስ የሆነው አምልኮ ጠላት በስጋ የሆነው አምልኮ ነው። ይሄ ስጋችን፥ በመንፈስ ለእግዚአብሔር የምናቀርበውን አምልኮ አይደግፈውም። ስጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በስጋ ላይ የሚቀዋወሙ እንደመሆናቸው መጠን፥ ይሄ ስጋችን በመንፈስ የሆነውን አምልኮአችንን የሚቃወም ነው። ስለዚህ የመንፈስ አምልኮ ጠላት፥ የስጋ አምልኮ ነው። የስጋ አምልኮ ፍጹም በመንፈስ ያልሆነ እና በስሜት ብቻ የሚመራ፥ ወይ በሙዚቃው ድምጽ እና በሰው ጩሐት ብዛት እየተጋጋለ፥ ከመንፈስ አምልኮ የሚያወጣ አምልኮ የመሰለ ግን አምልኮ ያልሆነ፥ መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ጋር የማይደርስ እና የእግዚአብሔር ቃል አምልኮ ብሎ የማያውቀው ነገር ነው። ከእውነተኛው አምልኮ ትኩረትን የሚስብ እና አይምⶂችንን በመሰብሰብ በመንፈስ ሆነን እውነተኛውን የመንፈስ አምልኮ በአምላካችን ፊት እንዳናቀርብ ተቃዋሚ ነው። ለዚህ ነው ሰው አጨበጨበ ወይንም ጉባኤው በጩሐት ተሞላ ማለት፥ እግዚአብሔር ተመለከ ብለን መደምደም የማንችለው። በአምልኮ ውስጥ አንጮህም፥ አናጨበጭብም እያልን አይደለም። ግባችን እና አላማችን ግን በመንፈስ በሆነው መገለጥ እና መደነቅ ውስጥ ወዳለው ጩሀት እና ጭብጨባ ጋር መድረስ ነው። አላማችን እግዚአብሔር እቀበለዋለሁ ወዳለው የአምልኮ ስርአት ውስጥ ገብተን፥ አምልኯአችንን ከስጋ ወደ መንፈስ አምልኮ ከፍ በማድረግ፥ መንፈስ ወደ ሆነው አምላካችን ጋር እንዲደርስልን ማድረግ ነው።  በመዝሙረ ዳዊት 51፡17 ላይ ሲናገር፥ “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” በማለት እንደሚናገረው፥ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መስዋእታችን፥ የተሰበረው መንፈሳችን፥ በፊቱ የምናዋርደው ልባችን እና በገዛ ፍቃዳችን ለእርሱ አምላክነት የምናስገዛው ማንነታችን ነው። መስዋእቱ እኛው እራሳችን ነን። በሮሜ መጽሐፍ ምእራፍ 12 ላይም እንደሚናገረው፥ ሕያው እና ቅዱስ መስዋእት አርገን በእግዚአብሔር ፊት የምናቀርበው፥ ሰውነታችንን እራሳችንን ነው። መስዋእቱ የመድረኩ መብራት እና ጭስ አይደለም። ጭስ የብሉይ ኪዳን መስዋእት ነው፥ የአዲስ ኪዳን መስዋእት አይደለም። እሱም ደግሞ አርቲፊሻል ጭስ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የመረጠው ጣፋጭ የሆነ የእጣን እና የመስዋእት ሽታ ነው። አሁን ግን መስዋእቱ ጭስ አይደለም። መስዋእቱ ግርግሩ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ መስዋእት ያልሆኑት ነገሮች፥ ትኩረታችንን በመውሰድ እውነተኛ የሆነውን መስዋእት በእግዚአብሔር ፊት እንዳናቀርብ እንዳያረጉን ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። እውነተኛ እና እግዚአብሔር የሚቀበለው አምልኮ በመንፈስ እና በእውነት ሆነን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ማንነታችን ነው። የተሰበረው መንፈሳችን፥ የተዋረደው ልባችን እንዲሁም በገዛ ፈቃዳችን ለእርሱ አምላክነት እና ፈቃድ የምናስገዛው መላው ሁለንተናችን ነው። የመንፈስ አምልኮ ጠላት እና ተቃዋሚ ደግሞ በስጋ ሆነን የምናደርጋቸው አምልኮ የመሰሉ ግን አምልኮ ያልሆኑት ነገሮች ናቸው።  እግዚአብሔርን ለማምለክ የተጠራነው በመንፈስና በእውነት ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ ግን አምልኮቻችን እውነትን የሚለቁበት እና ውሸትን የሚይዙበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ መዝሙሩ “እግዚአብሔር ሆይ ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብዬ አንተን ሳስብህ አድራለሁ” የሚል ዝማሬ ቢሆን፥ ይሄ ዝማሬ በእኛ የግል ህይወት ውስጥ እውነተኛ ነው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ካልሆነ ዝም ማለቱ ይሻላል እንጂ እግዚአብሔር ውሸትን፥ ያልሆነውን ነገር፥ የማናደርገውን ነገር እውነት ነው አምልኮ ነው ብሎ አይቀበለውም። አምልኮ በእውነት እና በመንፈስ ነው። እኛ ግን ብዙ ጊዜ በዝማሬ እግዚአብሔርን ስናመልክ፥ የምናመልከው እውነት ባልሆነ ወይንም በውሸት እና በስጋ ነው።  እንዴት ነው በመንፈስ ወደ ሆነው አምልኮ የምንገባው? ብለን ከጠየቅን፥ በተለይ በጉባኤው ውስጥ ሆነን በዝማሬ ስናመልክ፥ የአይንን መጨፈንን ጥቅም እንደዚህ የህይወቴ ምእራፍ የተረዳሁት ጊዜ የለም። በተለይ አሁን ባለንበት በዚህ ዘመን፥ መድረክ ላይ የምናያቸው አንዳንድ ነገሮች፥ በመንፈስ ወደሆነው አምልኮ የሚጋብዙ ሳይሆኑ፥ በስጋ ወደሆነው አምልኮ ወደመጋበዝ የሚያደሉ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው። ለምሳሌ ሰው መድረክ ላይ የሚሽከረከር ልዩ ልዩ ቀለም ያለው መብራት እና ጭስ እያየ እንዴት ነው ሀሳቡን መሰብሰብ እና እግዚአብሔርን ማሰብ እራሱ የሚችለው? እንዴት ነው በመንፈስ መሆን የሚችለው? አይን መጨፈን በተለያዩ ነገሮች ሀሳባችን ሳይወሰድ እና ሳይከፋፈል፥ ልናመልክ የቆምነውን እግዚአብሔርን ማሰብ እንድንችል ይረዳናል። በመንፈስ የምንሆነው፥  ሀሳባችንን በመሰብሰብ እና የምንዘምረውን መዝሙር እያስተዋልን በመዘመር ነው።  መዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 47፡7 ላይ ሲናገር “እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉስ ነውና፥ በማስተዋል ዘምሩ” ይላል። የምንዘምረውን መዝሙር አምልኮ አርገን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው፥ መዝሙሩን የምናውቀው እና ብዙ ጊዜ

Scroll to Top