ማንነት
Home Blog Book About Contact X Order Book ማንነት Audio እቤት ውስጥ ያደግነው፥ እኔ እና እህቴ ሆነን ነው። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው ብለው እነደሚናገሩት፥ ይሄ ተረትና ምሳሌ ትክክለኛ ተፈጻሚነትን ያገኘው እኛ ቤት ይመስላል። እኔና እህቴ ልጆች እያለን፥ ትንሽ እንኳን ሊቀራረብና ሊመሳሰል የማይችል የባህሪ ልዩነት ነበር የነበረን። አንዳንድ ቀን እንተያይና እንዴት እህትማማቾች ልንሆን እንደቻልን ሁለታችንም እንገረማለን። እሷ በተፈጥሮ ባህሪዋ ጸጥ ያለች፣ ከአዲስና ከማታውቀው ሰው ጋር ምንም አይነት ንግግር የማትፈልግ፥ አዲስ ሰዎችን ላለመተዋወቅ የተቻላትን ሁሉ ጥረት የምታደርግ፣ እቤታችን እንግዳ ሲመጣ፥ መኝታ ቤትዋ ገብታ በሯን በመቆለፍ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር እየሰራ ያለ ሰው መስላ ከስልኳ ጋር የምትጫወት፥ ግርግርና ስብሰባ የማትወድ፥ ሰዎችን ለመልመድና ነጻ ሆና ለማውራት ብዙ ጊዜያቶች የሚፈጁባት ልጅ ናት። እኛን ቤተሰቦቿን እራሱ የለመደችን፥ ከተወለደች ከብዙ አመታቶች በኃላ ነው። አንዳንድ ቀን አባታችን ለስራ ፊልድ ቆይቶ ሲመጣ፥ “አላውቅህም” በሚል አስተያየት ራቅ ብላ ቆማ እያየችው የፈለገ ቢለምናት የማትቀርብ ልጅ ነበረች። ትንሽ ልቧ የሚከፈተው ተመልሶ ሌላ ፊልድ ሊሄድ ሁለት ቀናቶች ሲቀሩት ነበር። እኔ እህታችሁ ደግሞ መጫወትና መሳቅ የግል ማንነቶቼ ናቸው። ጓደኞቼን የማስቅ፥ ቤት ውስጥ እንኳን የሆነ ጥፋት አጥፍቼ አባቴ ሊቆጣኝ ሲመጣ፥ ሊስቅ የሚችልባቸውን ነገሮች እያረኩ ቁጣና ንዴቱን በሳቅ አስለውጬ የማስመልስ ልጅ ነበርኩ። አዳዲስ ሰዎችን እንደመተዋወቅ የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም። እቤታችን እንግዳ ሲመጣ እንግዳውን ለማጫወት ካለሁበት ተፈልጌ የምጠራው እኔ ነበርኩ። ሳሎን ቤታችን ከእንግዳው ጋር በመቀመጥ፥ የማዋራቸው፣ ስለ ቤታችን የማያውቁትን ነገር በዝርዝርና በማብራሪያ በተደገፈ ሁኔታ የማስረዳ፥ አልፎም እንግዶቹን የማጫውትና የማስቃቸው እኔ ነበርኩ። ቤት ውስጥ ካኮረፍኩና ዝም ካልኩ፥ ቤቱ ዝም ስለሚል፥ መብራት እንደ ጠፋ ነበር የሚቆጠረው። ገና የዘጠኝና የአስር አመት ልጅ ሆኜ፥ እኩዮቼ የማይሄዱበት የእሮብ እሮብ የትልልቅ ሰዎች ጉባኤና መጽሀፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ የምሳተፍ፣ ልቤ ውስጥ የተፈጠረውን ጥያቄ እንዲያስረዱኝ ለመጠየቅ፥ የእድሜዬ ቁጥር አነስተኛነት አሳስቦኝ የማያውቅ፣ የገባኝን ደግሞ በተቻለኝ አቅም የማስረዳ ልጅ ነበርኩ። እኔ ለእህቴ፥ ከሌላ ፕላኔት የመጣሁ አስገራሚ ፍጥረት ነኝ። ታዲያ ቤተሰቦቼ በሙሉ ተመሳሳይ ባህሪ ስላላቸውና ከእነሱ ለየት ያለ ባህሪ የነበረኝ እኔ ስለነበርኩ፥ እነርሱ ትክክል የሆኑ፥ እኔ ደግሞ የተሳሳተ ጸባይ እንዳለኝ እያመንኩ የኖርኩባቸው ጊዜያቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከዚህም የተነሳ፥ እግዚአብሄር እንደ ቤተሰቦቼ ጸጥ ያልኩ እንዲያረገኝ እየለመንኩት የጸለይኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ። አሁን ላይ፥ በእድሜ መጨመርና እግዚአብሄር እየሰጠኝ ባለው ማስተዋል የተለወጡ አንዳንድ ባህሪያቶች ቢኖሩም፥ ምንም ብጸልይ እግዚአብሄር እስካሁን ከውስጤ ሊያወጣቸው ያልቻላቸውና ከተፈጥሮ ማንነቴ ጋር አብረው የተሰሩ ባህሪዎች አሉኝ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው አንድ የህይወቴ ወቅት ላይ የሁላችንም ተፈጥሮ፣ የሁላችንም ባህሪና ጸባዮቻችን በአጋጣሚ የተሰጡን እንዳልሆኑ እየተማርኩ የመጣሁት። በምታመልኩባቸው ቤተክርስቲያኖች ወይንም ባላችሁባቸው ህብረቶች ውስጥ፥ የሰዎችን ሁሉ ባህሪ አስተውላችሁ ካያችሁ፥ የሁሉም ሰው ባህሪ ልዩ ልዩ ነው። ፈጠን ያሉ፥ ሳቅና ጨዋታ የሚወዱ፥ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ማገልገል ስጦታቸው የሆነ፥ በህብረቶች ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ቀስ ያሉ፥ ዝም ያሉ፥ ፕሮግራሞች ላይ መጥተው ሰምተው ብቻ መሄድ የሚፈልጉ፥ ብዙ Activity-ዎች ውስጥ የማናያቸው ሰዎች ደግሞ አሉ። ከDNA-ያችን ጀምሮ፥ እስከ ጣት አሻራዎቻችን ድረስ እግዚአብሄር ተጠንቅቆ በልዩነት እኛን የሰራበት፥ የራሱ የሆኑ ትልልቅ አላማዎች አሉት። አንድ ጊዜ ጳውሎስ በገላትያ መጽሀፍ ምእራፍ አንድ ላይ፥ በህይወቱ ስላለፈባቸው ነገሮች፣ ጌታን ሳያገኝ በፊት ስለነበረው ማንነቶቹና ባህሪያቶቹ፥ እንዴት ቀናተኛ እንደነበረ፣ እንዴት አጥፊና አሳዳጅ እንደነበረ ከተናገረ በኋላ፥ “ነገር ግን እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ወዲያው ከስጋና ከደም ጋር አልተማከርኩም” በማለት ይናገራል። እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን በጳውሎስ ህይወት ለመግለጥ፣ የጳውሎስን እምነት እንጂ የጳውሎስን ባህሪና ማንነት በፍጹም አልቀየረም። “በእናቴ ማህጸን ሳለሁ የለየኝ” እንዳለው፥ እግዚአብሄር ገና ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ ጳውሎስን ሲለየው፥ ይሄንን ማንነት፥ ይሄንን personality የሰጠው፥ በህይወቱ መስራት የሚፈልገውን ነገር ስለሚያውቅ ነው። በራሱ በጳውሎስ ማንነት፣ በቆራጥነቱ፣ በመሰጠቱ፣ ያመነበትን ነገር ከማድረግ ወደሁዋላ በማይለው ማንነቱ ውስጥ እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን ገልጦታል። ጳውሎስ፥ ደፋር የሆነ፣ ለውሳኔዎቹና ላመነባቸው ነገሮች ነፍሱን እስከመስጠት የጨከነ፥ በአጠቃላይ አካባቢው ላይ ከነበሩ ሰዎች ለየት ያለ ባህሪ ያለው ሰው ነበር። የተለየ ማነነትና ተፈጥሮ የተሰጠው፣ የተለየ የእግዚአብሄር አላማ ህይወቱ ላይ ስለነበረ ነው። በጳውሎስ ማንነት ውስጥ፥ በጳውሎስ ባህሪና ተፈጥሮ ውስጥ የተገለጠው አስደናቂ የእግዚአብሄር የጸጋ አሰራር ታዲያ፥ እስከዛሬ ድረስ አለምን እየባረከ ይኖራል። ኢየሱስ ለአገልግሎቱ የሾማቸውን ሀዋሪያቶችን ስታይዋቸው፥ ሁሉም የተለያየ አይነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ዮሀንስን ብታዩት ፍቅርን የሚወድ የፍቅር ሰው ነበር። እርሱ የጻፋቸውን መጽሀፎች፥ አንደኛ ሁለተኛና ሶስተኛ ዮሀንስን ስታነቡ፥ አብዛኛው የጽሁፉ መልክቶች ስለ ፍቅር ወደ ማውራት የሚያደሉ ናቸው። ኢየሱስ ደረት ስር ጠጋ ማለት ይወዳል። ኢየሱስም ከሌሎቹ ለይቶ ዮሀንስን የሚያናግርበት፥ የፍቅር ቋንቋ አለው። እግዚአብሄር ከእኛ ጋር የሚነጋገረው፥ እኛን የሚያናግረው፥ እራሱ በሰጠን personality ውስጥ ነው። አይታችሁ ከሆነ፣ እግዚአብሄር ከአብርሀም ጋር የነበረው አይነት ግንኙነት አይደለም ከሙሴ ጋር የነበረው። እግዚአብሄር አብርሀምን ከወዳጆቹ ሁሉ ከለየው በኋላ፥ ወዳጅ ሆኖ ሲቆምለት እናያለን። ከወዳጄ ከአብርሀም የምሰውረው የለም እያለ፥ ሊያደርግ ያሰበውንና እርሱ እንኳን የማይመለከተውን ነገሮች ነበር ያወያየው የነበረው። እግዚአብሄር ከአብርሀም ጋር የነበረው አይነት ግንኙነት አይደለም ከሙሴ ጋር የነበረው። ሙሴን ያናግረው የነበረው ደግሞ፥ በክብሩ ደመና ውስጥ ነበር። ወደ ተራራ ላይ እየጠራ ነበር የክብሩን መገለጥ ያሳየው የነበረው። በእሳትና በደመና ነበር ይገለጥ የነበረው። መጀመሪያ እራሱ በኮሬብ ተራራ ላይ በእሳት ቁጥቋጦ ተአምራት ነው ወደ ራሱ አቅርቦ ልቡን የሳበውና በህይወቱ ሊያደርግ ያሰበውን አላማ በሙሉ የነገረው። እግዚአብሄር ከሙሴ ጋር የነበረው አይነት ግንኙነት አይደለም ከዳዊት ጋር የነበረው። ገና በእድሜው ማለዳ ላይ ነበር በብዙ ዝማሬና ቅኔ ከዳዊት ጋር ይነጋገር የነበረው። የእግዚአብሄርንና የዳዊትን ወዳጅነት ስናነብ፥ እግዚአብሄር ከሁሉ ነገሩ ይልቅ ከዳዊት ልብ ጋር ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት እንደነበረው እናያለን። መጀመሪያ እራሱ ከወንድሞቹ መካከል ሊመርጠው ሲነሳ፥ ሰው ፊትን ቢያይም እግዚአብሄር ግን ልብን እንደሚያይ በመናገር፥ ሊመርጠው እራሱ የቻለበት ምክኒያት ልቡ እንደሆነ ይናገራል። ዳዊትም በመዝሙሮቹ ውስጥ ልቡን በንጽህና በመጠበቅና በእግዚአብሄር ፊት ለማቅረብ የተቻለውን ሲያደርግ እናያለን። በህግና በተአምራቱ፣ በፍቅርና በምህረቱ ውስጥ እግዚአብሄር ከዳዊት ጋር ያደረገው ንግግር አስደናቂና የእኛንም ልብ እስከዛሬ ድረስ የሚነካ ታላቅ ነገር ነው። እግዚአብሄር ከእያንዳንዳችን ጋር ያለው ግንኙነት አይነቱ የተለያየ ነው። በሰጠን ማንነት ውስጥ ነው የሚያናግረን። በሰጠን ተፈጥሮ ውስጥ ነው communicate የሚያረገን። እግዚአብሄር እያንዳንዳችንን የሚያናግርበት የፍቅር ቋንቋ አለው። እነዚህ ቋንቋዎች ደግሞ የተለያዩ ናቸው:: ምክኒያቱ ደግሞ የሁላችንም የፍቅር ቋንቋ የተለያየ ስለሆነ ነው። ኢየሱስ ከሌሎቹ ሀዋሪያቶች በተለየ መልኩ ዮሀንስን ወደ ደረቱ ጋር የሚያስጠጋው፥ ዮሀንስ የፍቅር ሰው እንደሆነ፥ የዮሀንስ የፍቅር ቋንቋ መጠጋጋት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። በዮሀንስ የፍቅር ማንነት ውስጥ ታዲያ እግዚአብሄር ፍቅርን ለአለም ሰብኮበታል። የዮሀንስ ወንጌል፣ አንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዮሀንስ እያለ ፍቅርን ለአለም ጽፎበታል። ዮሀንስ ከዚህች ምድር ካለፈና ወደ ጌታ ከሄደ ስንትና ስንት ሺ አመታቶች ቢያልፉም፥ በዮሀንስ ማንነት ውስጥ በተገለጠው የእግዚአብሄር ፀጋ፥ እስከዛሬ ድረስ ፍቅርን እናነባለን፥ ፍቅርን እንማራለን፥ ፍቅርን እንሰበካለን። የጳውሎስን ጠንካራ ልብ ለማግኘት ደግሞ፥ እግዚአብሄር በደማስቆ መንገድ ላይ ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ ታላቅ ብርሀንና ድምጽ መገለጥ ነበረበት። ኢየሱስ የጳውሎስን ልብ ሊያገኝ የሚችለው፥ በደማስቆ መንገድ ላይ በልዩና ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ ተአምራት ሲገለጥ እንደሆነ ያውቃል። እግዚአብሄር በየት በኩል ቢመጣ ልባችንን እንደሚያገኘው ያውቃል። በዚህ እውቀቱ ነው ልባችንን አግኝቶ ያዳነን። እግዚአብሄር ተስፋ እንኳን ስንቆርጥ፥ በምን አይነት ተስፋ ልባችንን ካለበት ዝቅታ ውስጥ ሊያወጣው እንደሚችል ያውቃል። በምን በኩል ካለንበት ተስፋ መቁረጥ እንደሚያወጣን ያውቃል። አንዳችንን በሚያወጣን ተስፋ አይደለም ሌላችንን የሚያወጣን። የእያንዳንዳችንን ልብ ሊደግፍና ሊያነሳ የሚችለውን ተስፋ ጠንቅቆ ያውቀዋል። ምን እንደሚያስደስተን ያውቃል። ምን ልባችንን









