ጸሎት

መቼም ስለ ጸሎት የማያውቅ ሰው በዚህች ምድር ላይ አለ ብዬ አላስብም። ማለትም ሰው የክርስቶስ ተከታይ ባይሆን እራሱ የሆነ ነገር ተከታይ ነው። ወደ እግዚአብሔር ባይጸልይ እንኳን አምላክ የለም ብሎ ከሚያምን ሰው በስተቀር ወደሚያምንበት እና አምላክ ብሎ ወዳሰበው አካል ይጸልያል። ጸሎት አብዛኛው ሰው የሚያደርገው ነገር መሆኑ፥ ሰው ሁሉ በዚህች ምድር በሚኖረው በዚህ ሕይወት ውስጥ እርዳታ ፈላጊ መሆኑን እንድንረዳ ያደርገናል። አብዛኛው የዓለማችን ሕዝብ እንዲያውም ጸሎትን አማራጭ አድርጎ የሚያስበው፥ ጭንቀት እና ፍርሀት ውስጥ በገባ ሰአት ከእርሱ አቅም በላይ የሆነ አጣብቂኝ ውስጥ በገባ ሰአት ነው። 

ለእኛ በክርስቶስ አምነን የእግዚአብሔር ልጆች ለሆንን ሰዎች ግን ጸሎት ሲጨንቀን የምንሮጥበት ቦታ ብቻ ሳይሆን፥ ሁሉ ሰላም በሆነ ጊዜ፣ ሁሉ ደህና በሆነ ጊዜ ከአምላካችን ጋር የምናወራበት፣ እግዚአብሔርን ፍለጋ የምንሄድበት እና በየእለቱ ከምንወደው አምላካችን ጋር የምናደርገው የፍቅር ሕብረት ነው። ወደ ፊቱ እየመጣን የፍቅር መስዋእታችንን እና አምልኳችንን የምንሰጥበት የከበረ ስፍራ ነው። 

ጸሎትን ትርጉም ስጡት ከተባልን አብዛኞቻችን የምንሰጠው ትርጉም ይሄ ነው። ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ንግግር ነው። ልክ ከሰው ጋር ንግግር እንደምናደርገው ሁሉ፥ አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሰጠን የልጅነት መንፈስ ውስጥ ሆነን፥ አንድ ልጅ ከአባቱ ጋር በሚነጋገርበት ነጻነት ከአምላካችን ጋር እንነጋገራለን። ታዲያ ንግግር የምትለውን ቃል አስምሩልኝ። ንግግር በሁለት አካል መካከል በሚለዋወጡ ቃላቶች ውስጥ የሚደረግ የሀሳብ ልውውጥ ነው። አንደኛው አካል ብቻ ተናግሮ ጨርሶ የሚሄድበት አይደለም። ከተናገረ በኋላ የግዴታ እያናገረው ያለውን አካል ምላሽ እና ሀሳብ ይጠብቃል። እንደዚያ ሲሆን ንግግሩ ሙሉ ይሆናል። ጸሎት እኛ የምንናገርበት ብቻ አይደለም። እድል ከሰጠነው እና በትጋት ከፈለግነው እግዚአብሔርም ለእኛ የሚናገርበት ቦታ ነው። 

ይህም ደግሞ አምላካችን እግዚአብሔር ልክ በኤልያስ ዘመን የአህዛብ አማልክቶች እንደማይሰሙ እንደማይመልሱ እና እንደማይናገሩ በማሳየት ሕያውነቱን እንደገለጠው፥ ጆሮን የሰራ የሚሰማ፣ አንደበትን የፈጠረ የሚናገር አምላክ ስለሆነ ነው። ታዲያ ይሄ አምላክ እዛ የእነ ኤልያስ ዘመን ላይ ንግግሩን አልጨረሰም፥ ዛሬም ልክ ኤልያስን በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ ብሎ በወቅቱ ማድረግ ያለበትን እንደነገረው፥ ልክ ጊዜው ሲደርስ ደግሞ “አሁን ሂድና ለአክዓብ ተገለጥ” በማለት ኤልያስን እንደመራው፥ ዛሬም በፍጹም ልባቸው ለተከተሉት እና ለፈለጉት ሰዎች ይናገራል፣ ይመራል፣ በእያንዳንዱ የሕይወት ምእራፎች ውስጥ ያለውን ፈቃዱን በዝርዝር ይናገራል። 

የእግዚአብሔርን ምሪት፣ የእግዚአብሔርን ድምጽ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሀይል መለማመድ የምንጀምረው ታዲያ እግዚአብሔር እራሱ ጸልዩ ባለን መንገድ ወይንም እርሱ እንዳዘዘን ስንጸልይ ብቻ ነው። አንድንድ ጊዜ ጸሎት የሚመስሉ ነገር ግን ዝም ብለን እንደ ልማድ ብቻ የምናረጋቸው ካላረግናቸው ደስ የማይለን የእግዚአብሔርን ሀይል የማይገለጥባቸው ስጋዊ ልምምዶች አሉ። 

ጸሎት በየቀኑ የለመድናቸውን ቃላቶች መደጋገም አይደለም፣ ያማሩ ቃላቶች ስብስብ አይደለም፣ ጸሎት ችሎታ ወይንም የረጅም ጊዜ ልምድ አይደለም፣ ድምጽን ጮክ ማድረግም አይደለም፣  ሀይማኖታዊ ልምምድ እና ስርዓትም አይደለም። ይልቁንም ሕይወት ያለበት፣ እውነተኞች በመሆን ድካም ውስጥ ካለን፣ ድካማችንን በፊቱ አምነን በመቀበል ሀይልን የምንቀበልበት፥ ራሳችንን የምንሆንበት እና ልባችንን ከፈቃዱ ጋር በማስማማት ከአምላካችን ጋር ፍጹም የሆነውን ሕብረት የምናረግበት፣ ፈቃዱን የምናውቅበት፣ ፍቅራችንን የምንሰዋበት የከበረ ቦታ ነው። 


ስለ ጸሎት ስናስብ በመጀመሪያ ማሰብ ያለብን፥ እግዚአብሔር መንፈስ መሆኑን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ ወንጌል  ምእራፍ 4 ላይ ሲናገር “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ይላል:: ወዲያው ታዲያ ቀጠል አርጎ “የሚሰግዱለትም በእውነት እና በመንፈስ ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” በማለት ይናገራል። ከእግዚአብሔር ጋር ለማውራትም ሆነ እግዚአብሔርን ለማምለክ ስንቆም፥ መጀመሪያ መረዳት ያለብን እግዚአብሔር መንፈስ መሆኑን ነው። በመሆኑም ከእርሱ ጋር ማውራት፣ ሕብረት ማድረግም ሆነ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መገለጦች ጋር በመድረስ እርሱን ማምለክ የምንችለው በእውነት እና በመንፈስ መሆንን ስንማር ብቻ ነው። የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ምእራፍ 1፡10 ላይ ዮሐንስ ሲነግረን እንደዚህ ይላል “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ..” ይላል።  እግዚአብሔር እየተናገረ ያለውን የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት የምንጀምረው፣  በመንፈስ መሆንን መለማመድ ስንጀምር ብቻ ነው። ሌላ ተጨማሪ ቃል ደግሞ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምእራፍ 1 ከቁጥር 10 ጀምሮ እንዲህ በማለት ይናገራል። 


“መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።” 

በጸሎት ውስጥ እውነተኛ የሆነውን ሕብረት ከእግዚአብሔር ጋር ለማድረግ፥ ድምጹን ለመለማመድ እና ምሪት በምንፈልግባቸው የሕይወታችን ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ምሪትን ለማግኘት፥ በመንፈስ መሆንን እራሳችንን ማስለመድ ያስፈልገናል። እንዴት ነው በመንፈስ መሆንን የምንማረው ብለን ከጠየቅን፥ የሚረዱንን ጥቂት ነጥቦች እስኪ እንመልከታቸው። 

  1. ልባችንን መመርመር፡- መቼም እግዚአብሔር እራሱ በቃሉ ከነገረን ዋና ዋና ነገሮች አንዱ ከመጸለያችን በፊት ውስጣችንን መመርመር እንዳለብን ነው። ከሰዎች ጋር ቅሬታ፣ ቂም እና ጥላቻ ካለብን፥ ያንን መጀመሪያ መፍታት እንዳለብን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ማለት እንዳለብን፥ ጉዳያችንን መጨረስ ካለብን ሰዎች ጋር መጨረስ እንዳለብን፣ በእርሱ ፊት ለጸሎትም ሆነ ለአምልኮ ከመቆማችን በፊት ልባችን በፍጹም ፍቅር እና ይቅርታ ውስጥ መሆን እንዳለበት በቃሉ ነግሮናል። እንዲያውም ሰዎችን ይቅር አለማለታችን እግዚአብሔር የእኛን በደል ይቅር እንዳይለን ሊያደርግ የሚችል ከባድ ነገር መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል። ስለዚህ ለጸሎት ከምንዘጋጅባቸው ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱ ከእነዚህ እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ነገሮች ሁሉ ልባችንን ማጽዳት ነው።
  2. እግዚአብሔርን በሙሉ ትኩረት ማሰብ:- በመንፈስ ለመሆን ከሚረዱን ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱ፥ በትኩረት ወይንም ባልተከፈፋፈለ ሀሳብ እግዚአብሔርን ማሰብ ነው። ይሄ የታወቀ የሚመስለን ግን ጥቅሙ ያን ያህል ስላልገባን፥ የሚገባውን ቦታ ያልሰጠነው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። እስኪ አንድ ጥያቄ ራሳችንን እንጠይቅ፥ ከሰዎች ጋር ስንጸልይ፥ መቼ ነው የሰዎቹን የጸሎት ችሎታ መገምገም ትተን እግዚአብሔር ላይ ትኩረት በመስጠት የጸለይነው? መቼ ነው በህብረት ዝማሬዎቻችን ላይ የአዘማሪዎቹን የዝማሬ ችሎታ ወይንም ብቃት መገምገም ትተን ዝማሬው ውስጥ ያሉትን እያንዳንዱን ቃላቶች በማስተዋል፥ አምላካችንን ብቻ እያሰብን የዘመርነው? መቼ ነው ስብከት ለማቅረብ ፊታችን የቆመውን ሰው የአሰባበክ ችሎታ መገምገም ትተን፥ በሰባኪው ውስጥ እግዚአብሔር ሊናገረን የወደደውን ለማስተዋል ልባችንን አምላካችን ላይ ብቻ ያደረግነው? አብዛኛውን ጊዜ እንዲያውም ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠን ሀሳባችን ሌላ ሌላ ቦታ ላይ ስለሆነ አሜን በማይባልበት የተሳሳተ ቦታ እራሱ አሜን ስንል ወይንም ሰዎች ሲሉ አጋጥሞን አያውቅም?  ብዙ የምናረጋቸውን ነገሮች በማስተዋል ከተመለከታችሁ፥ ለምናረጋቸው ነገሮች ምንም ትኩረት አንሰጥም።

    አንድ ቀለል ያለ ምሳሌ ብንመለከት፥ አንድ በጣም ከምናከብረው ሰው ጋር ምሳ ወይንም እራት ለመብላት ብንቀጣጠር፥ ያንን ሰው ካገኘነው በሁዋላ ለዚያ ሰው ክብር ስንል ከምንሰጠው ቀዳሚ እና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱ ሙሉ ትኩረታችንን ነው። ያንን ሰው አስቀምጠን በስልካችን ድራማ አናይም። ወይንም ሲጮህ የሚውለውን ስልካችንን አንስተን ከሌላ ሰው ጋር ሌላ ጨዋታ አንይዝም። ወይንም ሌላ ሌላ ነገር እየሰራን ለዚያ ፊታችን ለተቀመጠው ለምናከብረው ሰው የተከፋፈለ ትኩረት አንሰጠውም። ይልቁንም ያ የምናከብረውን ሰው አይን አይኑን እያየን ሙሉ ትኩረታችንን ወደዚያ ሰው አርገን በአክብሮት እናወራለን። ለአንድ ለምናከብረው ሰው ይገባዋል ብለን የምንሰጠውን ነገር፥ እንዴት ለእግዚአብሔር አንሰጠውም? አንድ የምናከብረው ሰው ይገባዋል ብለን የምናስበው ነገር፥ እንዴት እግዚአብሔርን አይገባውም? እግዚአብሔር በሚልክያስ መጽሐፍ ላይ ስለ መስዋእት ሲናገር እንዲህ አለ “እስኪ ይሄን ያመጣኸውን አንካሳ እና እውር መስዋእት ለአለቃህ አቅርበው። ለአለቃህ ታቀርበዋለህ?” በማለት ለእርሱ የምንሰጠውን ነገር፥ ለሰዎች ከምንሰጠው ነገር ጋር በማወዳደር ተናግራል። እግዚአብሔር ይሄንን የተናገረው፥ ብዙ ልማዶቻንን በማስተዋል ብንመለከታቸው፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰዎችን ስለምንፈራ እና ስለምናከብር ነው።

    ለጸሎትም ሆነ ለአምልኮ በአምላካችን ፊት ስንሆን፥ አስቀድመን ማድረግ ያለብን ሙሉ ትኩረታችንን ከሌሎች ነገሮች ላይ አንስተን በአምላካችን ላይ ማድረግን እራሳችንን ማስለመድ ነው።  ስለ ሌሎች ነገሮች ማሰባችንን ትተን፥ ስለ እግዚአብሔር ብቻ ማሰብ፥ ታላቅነቱን በማሰብ፣ ክብሩን በማሰብ፣ ሀይሉን በማሰብ፣ ታማኝነቱን በማሰብ፣ ፍቅሩን እና ምህረቱን በማሰብ እና ይሄ አይምሮአችንን ወይንም የእውቀት ክፍላችንን ስለ እግዚአብሔር ባለን እውቀት እየሞላን፥ ለእግዚአብሔር 100% ፐርሰንት ትኩረታችንን እየሰጠን እናስበዋለን። ይሄ ጊዜ ስለ ስራችን የምናስብበት ጊዜ አይደለም፣ ስለ ቤተሰቦቻችን፣ ስለ ቀን ውሎአችን እና ስለገጠሙን ነገሮች ሌላው ቀርቶ ስለ አገልግሎታችን እራሱ የምናስብበት ጊዜ አይደለም። በቃ ስለ እግዚአብሔር ብቻ የምናስብበት የፍቅር ጊዜያችን ነው። ወገኖቼ እግዚአብሔርን እንደ ማሰብ ደስታ የሚሰጥ ምንም ነገር የለም። እንዲያውም አንድ ቃል ትዝ አለኝ። “እግዚአብሔርን አሰብኩት አለና ደስም አለኝ” በማለት በመዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 77፡3 ላይ አሳፍ በጻፈው መዝሙር ላይ ይናገራል። ሁላችንም አማኞች ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ አለ። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ወደ ላቀ ሕብረት ውስጥ የሚገቡት ሰዎች ግን በፍጹም ትኩረት የሚፈልጉት ሰዎች ናቸው።

    ለአምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ስንቆምም ትኩረታችንን መድረክ ላይ ካሉት ሰዎች፣ አሁን ደግሞ በዘመናችን መድረኮች ላይ ከምናያቸው ካሜራዎች ፎቶ ግራፎች፣ አላስፈላጊ እና ትኩረት ሳቢ ከሆኑ እስክሪኖች እንዲሁም የመድረክ ጭሳጭሶች ላይ አንስተን እግዚአብሔርን ብቻ በማሰብ በመንፈስ እና በእውነት መሆንን ልንለማመድ ይገባል። ይህም ደግሞ እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ የሚሰግዱለት እና የሚያመልኩት ሁሉ በስጋ ሳይሆን በመንፈስ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ኢየሱስ እራሱ በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 4 ላይ በቃሉ ላይ ስለነገረን ነው። ጠላት በዚህ ዘመን አምላካችን ላይ እንዳናተኩር ሀሳባችንን በብዙ ነገሮች እየከፋፈለ ያለው እንዲሁም የሰዎችን ትኩረት ገንዘብ አድርጎ እይሰራበት ያለው በሰዎች ትኩረት ውስጥ ያለው ሀይል ስለገባው አይመስላችሁም? እኛ ግን የመረጥነው ነገር ላይ የማተኮር መብታችን እስካልተወሰደብን ድረስ፥ ትኩረታችንን ለሚገባው አምላክ እንደ መስዋእት አርገን ብናቀርበው ለሕይወት የሚሆንን ብዙ ነገር እናተርፋለን።
  3. ልንጸልይ በእግዚአብሔር ፊት ከመሆናችን በፊት ማድረግ ያለብን ሌላኛው ነገር ደግሞ በፍጹም መገዛት ውስጥ በመሆን ሙሉ ፈቃዳችንን ለእርሱ መስጠት ነው። ይህም ማለት ከእኛ ፍላጎት ወይም ፈቃድ ይልቅ እግዚአብሔር በሕይወታችን ይሁን ያለው የእርሱ ፈቃድ እንደሚልቅ እና እንደሚበልጥ በመረዳት፥ ለዚያ ፈቃዱ እሺ ማለት፣ ይሁን ማለት፣ እጅ መስጠት እና በሙሉ ልባችን ከፈቃዱ ጋር መስማማት ነው። እኛ መልካም ነው ብለን ከያዝነው መንገድ ይልቅ፥ እግዚአብሔር ያለው እንደሚበልጥ እንደሚሻል እና እንደሚልቅ፥ የእርሱ ሀሳብ ደግሞ ለእኛ ሁልጊዜ መልካም እንደሆነ በመረዳት እና ሙሉ ለሙሉ ፈቃዳችንን በመስጠት ልባችንን በዚህ እውነት እና ሀሳብ ውስጥ ማድረግ ነው። ወገኖቼ ይህቺን በደምብ አስተውሉልኝ፥ ጸሎት ማለት እኛ የፈለግነውን ነገር ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔርን ለማሳመን የምናደርገው የቃላት ድርድር አይደለም። ይልቁንም ልባችንን ከፈቃዱ ጋር የምናስማማበት ስፍራ ነው። እንዲያውም ከእኛ ፍላጎት እና ፈቃድ በላይ ኢየሱስ ሲናገር የአባቴን ፈቃድ ማድረግ ለእኔ ምግቤ ነው እንዳለው፥ የእርሱ ፈቃድ እንዲሆን አጥብቀን በመሻት የእኛን ፈቃድ ከፈቃዱ በታች የምናስገዛበት የመገዛት ስፍራ ነው። መዝሙር ምእራፍ 100 ላይ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደምንገባ ሲናገር፥ ወደ ደጆቹ በመገዛት መግባት እንዳለብን ይናገራል። ወደ እግዚአብሔር ደጆች እገባለሁ ያለ ሰው፥ ለእግዚአብሔር አምላክነት፣ ገዢነት እንዲሁም ፈቃድ መገዛት ይኖርበታል።

    ለዚህ ነው ለጸሎት በፊቱ ስንሆን፥ የእርሱ ፈቃድ የበላይ እንደሆነ እንዲሁም ደግሞ ፈቃዱ ፍጹም መልካም እንደሆነ አምነን መጀመር ያለብን። እግዚአብሔር የእኛ ጉዳይ አስፈጻሚ ወይንም እኛ የፈለግንበት ቦታ ለመድረስ የምንጠቀምበት መጠቀሚያችን ሳይሆን፥ እርሱ ከዚህች አጭር ምድራዊ ቆይታችን ባሻገር ዘላለማችንን አሻግሮ መመልከት የሚችል አምላክ ስለሆነ፥ መልካም የሆነውን ካልሆነው የመለየት ሙሉ እውቀት ስላለው እንዲሁም ደግሞ በጣም ስለሚወደን፥ እኛ ለጊዜው መልካም የመሰለንን ነገር አይሆንም እንዲለን ሙሉ ፈቃዳችንን የሰጠነው ሉአላዊ አምላክ ነው። ለዚህ ነው ምንም ነገርን ከእግዚአብሔር ከለመንን በኋላ “እግዚአብሔር ሆይ የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” በማለት ፈቃዳችንን ሙሉ በሙሉ በፈቃዱ ስር ማስቀመጥ ያለብን። ከኢየሱስ የተማርነውም ይሄንን ነው። ኢየሱስ በሞት እና በመከራ ጭንቅ ውስጥ ሆኖ እንኳን “ብትወድ ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ” በማለት ቢጸልይም ወዲያው በመቀጠል እንዲህ ማለትን አልረሳም “ነገር ግን አባት ሆይ የእኔ ፈቃድ ሳይሆን ያንተ ፈቃድ ትሁን” አለ፡፡ እንኳን ምቾት ውስጥ ሆነን ቀርቶ፥ መከራና ጭንቅ ውስጥ ሆነን እንኳን የእግዚአብሔር ፈቃድ በምናልፍባቸው ጭንቆች ውስጥ እንዲከናወን ወደ መፈለግ ማደጋችን፥ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ፍላጎት ነው።

    ኢየሱስ ፍቃድህ ቢሆን ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ ብሎ እግዚአብሔርን ጠይቋል፥ መጠየቃችን ምንም ስህተት የለውም። ጽዋው ከኢየሱስ እንዲያልፍ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም። ኢየሱስ ምንም ከባድ ቢሆንም፥ ያንን የመከራ ጽዋ በመጠጣት የአባቱን ፍቃድ ለማድረግ ተስማምቷል። ምንም ጽዋው ከእርሱ ባያልፍም ግን፥ ኢየሱስ ወደ አባቱ የጭንቀትን ጸሎት ከጸለየ በኋላ፥ እግዚአብሔር የሚያበረታ መልአክን እንዳዘዘለት በዚያው ክፍል ላይ ይናገራል። አያችሁ ጸሎት ያለንበትን ሁኔታ ባይቀይር እንኳን፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በምናልፍባቸው ፈተናዎች እና መከራዎች ውስጥ የሚያበረታ መልአክ እንዲላክልን ያስደርጋል። ጸሎት ወይ ያለንበትን ከባድ ሁኔታ ያስቀይራል፥ ወይንም ደግሞ ከእኛ የመታገስ እንዲሁም የመቻል አቅም በላይ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ሀይል እና ብርታት እናልፈው ዘንድ የሚያስፈልገንን ጸጋ እንድንቀበል ያደርጋል። ስለዚህ በመከራ ውስጥ ስንሆን መጸለይ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። የእግዚአብሔርም ቃል ማንም መከራን የሚቀበል እርሱ ይጸልይ በማለት የሚናገረው፥ ሰው በሚያልፍበት መከራ ውስጥ፥ መፍትሄን መድሀኒትን እና እርዳታን በጸሎት ውስጥ ስለሚያገኝ ነው። ታዲያ በዚህች ምድር ስንኖር በሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ውስጥ በጭንቀትም ሆነ በሰላም ጊዜ፥ በድካምም ሆነ በብርታት ጊዜ ስንጸልይ፥ ልባችን ሁልጊዜ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን ወደመፈለግ ማደግ አለበት። 
  4. ሌላው ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ለማድረግ ወይንም ለጸሎት በፊቱ ስንሆን እርግጠኞች መሆን ያለብን ዋና ነገር በእምነት ውስጥ መሆናችንን ነው። ያለ እምነት የሆነ የትኛውም ነገር እግዚአብሔርን ደስ እንደማያሰኘው ቃሉ ይናገራል። በያእቆም መልእክት ላይ፥ የሚለምን ሰው በምንም ሳይጠራጠር በእምነት መለመን እንዳለበት፥ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተገፋና የተነቃነቀ የባሕር ማእበልን እንደሚመስል ይናገራል።  መቼም እምነት እራሱን የቻለ ትልቅ ርእስ ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ቃል ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ ብንመለከት፥ ከእምነት ውጪ ወደ እግዚአብሔር አለም ውስጥ የምንገባበት ሌላ መንገድ እንደሌለ እንረዳለን። ሌላው ቀርቶ፥ ኢየሱስ የከፈለልንን ዋጋ አውቀን የእግዚአብሔር ልጆች ወደመሆን ክብር የመጣነው፥ እግዚአብሔር በሰጠን እምነት ውስጥ ነው። ልዩ ልዩ ድንቅና ተዓምራቶችን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስንመለከትም በእምነት ውስጥ ያለፈው የእግዚአብሔር ሀይል ውጤቶች መሆናቸውን እንገነዘባለን። በአጭሩ እንዲህ በማለት እንዝጋው እግዚአብሔር ምላሽ መስጠት የሚወደው ጸሎት ለሚመስሉት የተደጋገሙ ቃላቶቻችን አይደለም፥ ለእምነታችን ነው።
  5. ዝምታ፦ ብዙ ጊዜ ጸሎት ላይ ነው ብለን የምናስበው፥ እየተናገረ ያለን ሰው ነው። ከመጸለያችን በፊት  ልባችንን ማዘጋጀት እና ሙሉ ትኩረታችንን ለእግዚአብሔር ለመስጠት እንዳለብን ተነጋግረናል። የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው የምላስ መልስ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። በማለት በምሳሌ ላይ እንደሚናገረው፥ እግዚአብሔር መልስ የሚሰጠው ለጸሎት ችሎታችን ወይንም ባለማስተዋል ለምናረጋቸው የቃላት ድርደራዎቻችን ሳይሆን፥ ለተዘጋጀ እና እርሱን ለፈለገው ልባችን ነው። ስለዚህ እርሱን በሚወድ እና በሚፈልግ ልብ ውስጥ ሆነን፥ ትኩረታችንን በሙሉ በእርሱ ላይ ብቻ አርገን፥  ሙሉ ልባችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ እያስገዛን፣ በሙሉ መሰጠት ውስጥ ሆነን ደጁን እየጠናን ጸጥ ብለን የእግዚአብሔርን ድምጽ እንጠብቃለን። ወገኖቼ እግዚአብሔርን ደጅ ላይ በመቆየት እንደመጠበቅ ያለ አስደሳች ነገር በዚህች ምድር ላይ የለም። ምክኒያቱም መጠበቃችንን በሚበልጥ ካሳ እንደሚከፍለው እና እንደሚክሰው ስለምናውቅ ነው። እርሱን ተስፋ ያደረጉ እንዳማያፍሩ ስለምናውቅ ነው። በዚህ ውስጥ ነው እውነተኛ የሆነውን ሕብረት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምናደርገው። በጸጥታ ውስጥ ድምጹን መለማመድ እንጀምራለን። በልባችን እርሱን አጥብቀን እየፈለግን በዚያ መንፈስ ውስጥ ስንሆን እግዚአብሔር ወደ ጸሎት መሰዊያችን ወደ ጥበቃና እርሱን ወደሚፈልገው ልባችን ይመጣል። እግዚአብሔር መልስ የሚሰጠው ለረሀብ ነው። የሚያጠግበው ረሀብን ነው። እግዚአብሔር የሚገኘው በፍጹም ልባቸው ለፈለጉት ሰዎች ብቻ ነው።

    አንዳንድ ጊዜ በአምላካችን ፊት ስንሆን የአንደበታችን ቃል ላያስፈልግ እራሱ ይችላል። አንደበታችን ምንም ቃል ሳይናገር፥ በፍጹም ጸጥታ ውስጥ ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር ሕብረት ማድረግ ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ እኮ በጣም ከምትወዱት፣ ሁልጊዜ አብራችሁ ከምታሳልፉት እና እጅግ በጣም ከምትቀርቡት ሰው ጋር ስትሆኑ ቃል እና ንግግር አስፈላጊ ሆኖ የማይገኝባቸው ጊዜያቶች አሉ። ዝም ብላችሁ እዚያ ሰው አጠገብ ተቀምጣችሁ፥ ያ ሰው አጠገባችሁ መሆኑን፣ አብሯችሁ መሆኑን ኢንጆይ ታረጉታላችሁ። ሁለታችሁም ዝም ብላችኋል ግን ከሚያወሩ ሰዎች በላይ ልትግባቡ ትችላላችሁ። አንደበታችሁ ምንም ባይናገርም ልባችሁ ተግባብቷል። ፍቅራችሁ ተግባብቷል። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዲህ አይነት ብዙ ጊዜያቶችን ማሳለፍ ይቻላል። ጸጥ ብላችኋል፥ በፍጹም ጸጥታ ውስጥ ሆናችሁ በልባችሁ ከእርሱ ጋር በምታደርጉት ሕብረት ውስጥ ፈቃዱን ታውቃላችሁ፥ ምሪቱን ታውቃላችሁ፥ ፍላጎቱን ታውቃላችሁ፥ በአንዳንድ የእርሱን ምሪት በምትፈልጉባቸው ጉዳዮች ውስጥ ወዴት አቅጣጫ እንድትጓዙ እንደፈለገ ታውቃላችሁ። የጸሎት ስፍራችሁ ጸጥ ብሏል፥ እናንተም ጸጥ ብላችኋል ግን የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ እየሰማችሁ ነው። እግዚአብሔር ሲናገር እየሰማችሁ ነው። የእግዚአብሔርን ምሪት በመፈሳችሁ ውስጥ እየሰማችሁ ነው። የምትሰሙት በተፈጥሮ ጆሮአችሁ አይደለም። በመንፈሳችሁ ውስጥ ነው። ከዚህ የተነሳ ትረጋጋላችሁ፣ ሰላም እና ደስታን የተሞላችሁ ትሆናላችሁ። ይሄ ነው ጸሎት ማለት እኛ ለእግዚአብሔር የምንናገርበት፥ የእርሱን ድምጽ ፍለጋውን ደግሞ የምንከተልበት።

    በመጨረሻም፥ መንፈስ ከሆነው ከአምላካችን ጋር እውነተኛውን ሕብረት በማድረግ ድምጹን እና ሀይሉን ወደምንለማመድበት አለም ውስጥ በፍጥነት ለመግባት የሚያስችለንን አንድ ሚስጥር ይሄ ነው። ጸሎት ስንጀምር፥ በምስጋና እና በአምልኮ እንጀምር። እግዚአብሔር ይወደዋል፥ ይደሰትበታል፣ ይከብርበታል፣ በእውነተኛ ልባችን ሆነን ከልባችን ስናመሰግነው፥ ምስጋናችንን ለመቀበል ደስ በሚለው ሕልውናው ወደ ጸሎት መሰዊያችን ይመጣል። ምስጋና እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል፣ ይስበዋል። አምልኮ ቅዱስ የሆነውን ሕልውናውን ይጠራዋል። ቶሎ ከእርሱ ጋር የሚያገናኘን አቋራጭ መንገድ ነው። ከራሳችን የስጋ ሀሳቦች እየወጣን መንፈስ ወደሆነው ወደ አምላካችን አለም ውስጥ ቶሎ እንድንገባ የሚረዳን አቋራጭ መንገድ ነው። 



"Our true success in this life is being able to fulfill the purpose we were created for!"

for the Kingdom through Christ !

©2026, Hana Elias. All Rights Reserved

Scroll to Top