እድገት
Audio
መቼም የሕይወት ዘመን ተማሪ እንደመሆኔ መጠን፥ በየደረስኩበት መንገድ የምማራቸውን ነገሮች ለሰዎች ማካፈሌ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ሀሳብ እንደሆነ አውቃለሁ። እስከዛሬ በጽሁፍ ወደ እናንተ ካደረስካቸው መልእክቶች ውስጥ የእኔን ሕይወት ያለወጠ፣ እኔን ያላስተማረ እና አይምሮዬን ያላደሰ፣ የሕይወቴ አካል አድርጌው ለመኖር የማልሞክረው ጽሁፍ የለም ብዬ በድፍረት መናገር እችላለሁ። የማካፍለው የደረስኩበትን ብቻ ነው። የምሰጠው የተቀበልኩትን ብቻ ነው። ታዲያ ሰሞኑን አስብና አሰላስል የነበረውን እንዲሁም ነፍሴ የተመከረችበትን እውነት ለትንሽ ሰው እንካን ጥቂት የሚጠቅም ነገር ከተገኘበት ብዬ ልክ እንደ ወትሮው ዛሬም በጽሁፌ ይዤላችሁ እመጣ ዘንድ መልካም ሆኖ ታየኝ። አስብ የነበረው ስለ ማደግ ወይንም ስለ እድገት ነው። በየቀኑ በዙሪያችን እንደምንመለከተው ሕይወት ያለው ነገር በሙሉ ያድጋል። አንድ ልጅ ይወለድ እንጂ ከበላና ከጠጣ ማደጉ አይቀርም። ታዲያ አንድ ልጅ ከተወለደ እና የሚያስፈልገውን ምግብ ካገኘ እንደሚያድገው ሁሉ፥ ዳግም የመወለዳችን ዋናው ምልክት በሕይወታችን የሚታየው እድገት ነው። የምናድገው ስለተወለድን ነው፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም ስለተወለድን ነው። የተወለደ ነገር ሁሉ ሕይወት ያለው ነገር እንደሚያድግ ሁሉ፥ ልክ እንዲሁ ዳግም የተወለድነው ለማደግ ነው። እያደግን ካልሆነ ምክኒያቱ ከሁለት አንዱ ነው። ወይ ከነጭራሹ አልተወለድንም ወይንም ደግሞ ለማደግ የሚያስፈልገንን አስፈላጊ ምግብ እየተመገብን አይደለም ማለት ነው። የማይመገብ ሰው ደግሞ ቀስ እያለ ወደ ሞት እንደሚሄድ ሁሉ፥ አለመመገብ በጊዜ ውስጥ መንፈሳዊ ሞትን ሊያመጣ ይችላል። በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን ድነናል ወይንም ዳግም ተወልደናል ካልን፥ በሕይወት ለመቆየት ምግብ የመብላታችን ነገር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እድገታችንን በቀጥታ ያያያዘው የእግዚአብሔርን ቃል ከመመገብ ጋር ስለሆነ ነው። መወለድ እና ማደግ ሁለት የማይለያዩ ነገሮች ናቸው። የተወለደ እና ህይወት ያለው ነገር በሙሉ እንደሚያድግ ሁሉ፥ ዳግም በክርስቶስ አምኖ የተወለደ ሰውም ልክ እንደዚያው በመንፈሳዊ ሕይወቱ ማደግ አለበት። የእግዚአብሔርም ቃል መዳናችንን እና ማደጋችንን ለያይቶ አያየውም። እንዲያውም 1ኛ ጴጥሮስ ምእራፍ 2፡1-3 ላይ ሲናገር እንዲህ ይላል። “ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” ይላል። ጌታን ተቀብዬ ድኛለሁ ከዚያ እንደፈለኩ እኖራለሁ የሚባል ነገር የለም። የዳንነው ለማደግ ነው። በእግዚአብሔር ቤት በቆየንበት ጊዜ ልክ እግዚአብሔር እድገትን ከእኛ እንደሚጠብቅ የሚያስተምረንን አንድ ክፍል ከእግዚአብሔር ቃል ላንብብላችሁ።
“ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።” (እብራውያን 5፡12-14)
ታዲያ ማደጋችን ከመዳናችን ጋር በቀጥታ የሚገናኝ እና አማራጭ የሌለው ነገር ከሆነ፥ ለማደግ የሚረዱንን 3 ዋና ዋና ነገሮች ከታችን እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን።
1ኛ የእግዚአብሔር ቃል፦ ከላይ እንዳነበብነው የእግዚአብሔር ቃል ሀሳብ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እድገታችንን በቀጥታ የሚያያይዘው የእግዚአብሔርን ቃል ከመመገብ ጋር ነው። ለማደግ የምንፈልግ ከሆነ ለእግዚአብሔር ቃል ትልቅ ቦታ መስጠት ይኖርብናል። በየቀኑ የሚመቸንን ቋሚ ጊዜ ፈልገን የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ እና በማጥናት እንዴት አርገን ከህይወታችን ጋር አገናኝተን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ማሰላሰል አለብን። ቤተክርስቲያን ስንሄድ የእግዚአብሔር ቃል ሲነገር ቁጭ ብለን ማዳመጥ፣ ሶሻል ሚዲያዎቻችን ላይ ደግሞ እንዲያው ዝም ብሎ የማይጠቅመንን ነገር ከምናይበት፥ ጥሩ ጥሩ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች የሚያስተምሩትን ትምህርቶች መስማት፣ እነዚህ ሁሉ እኛን በማሳደግ ፍጹምና ለበጎ ስራ የተዘጋጀን እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን መጽሐፍ በማወቅ እያደግን የምንማርባቸው፣ የምንገሰጽባቸው፣ ልባችንን የምናቀናባቸው እንዲሁም የጽድቅን ምክር የምንመከርባቸው መንገዶች ናቸው። አንድ ህጻን እስኪ ልደግ ብሎ አይበላም። እየበላ ሲሄድ ግን እራሱ በማያውቀው ሁኔታ በየቀኑ ቁመቱ ሲጨምር፣ እና ሰውነቱ ሲያድግ እንመለከታለን። ኦ ይሄ ልጅ ዛሬ ነው በጣም ያደገው አንልም። ያ ህጻን አብሮን እራሱ አንድ ቤት እየኖረ መቼ ቁመቱ እና ሰውነቱ ጨምሮ እንዳደገ ሳናውቀው እድገቱን እናየዋለን። ዛሬ ነው ያደገው ብለን ያደገበትን ቀን በትክክል አናየውም፥ ሲመገብ ግን እናየዋለን። በህይወት መቆየቱ እና እድገቱ፥ የመብላቱ ውጤት እንደሆነም እናውቃለን። ለእግዚአብሔርን ቃል ቦታ እየሰጠን በየቀኑ ስንመገብ፥ መመገባችን አንተው እንጂ እድገታችን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነገር አይደለም።
የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ እና ለማሰላሰል ጊዜ መስጠት፥ ፊልም እንደ ማየት ወይንም ሌሎች የምንወዳቸውን ነገሮች እንደማድረግ ለስጋችን አስደሳች ላይሆን ይችላል። ግን ሌሎች ነገሮችን ለመዝጋት እና ለመጨከን መወሰን አለብን። የውሳኔ ሰው መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። ለማንበብ ፍላጎት የሚባል ነገር አጥተን የምንቸገር ከሆንን ደግሞ ግልጽ ሆነን እግዚአብሔር ይሄንን ረሀብ እንዲሰጠን መጸለያችን ትልቅ ለውጥ ያመጣል። እኔ የራሴን ህይወት ስመሰክርላችሁ፥ ከድሮም እግዚአብሔር ሰጥቶኝ እና ረድቶኝ መጸለይና መዘመር እወዳለሁ። ረጅም ሰአት ብጸልይና ብዘምርም የእግዚአብሔርን ቃል የማንበብ ግን ምንም ፍላጎት አልነበረኝም። ታዲያ ቃሉን ማንበቤ እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ሲገባኝ፥ ግልጽ ሆኜ እግዚአብሔር ቃሉን የማንበብ ፍላጎት እንዲሰጠኝ ለመንኩት። ታማኝ ስለሆነ ከምንለምነውና ከምናስበው እጅግ አብልጦ የሚሰጠው አምላክ፥ በልቤ የቃሉን ረሀብ ላከ። አሁን ላይ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ማንበብ እና ማሰላሰል የሚያስደስተኝ ነገር የለም። ድሮ ቸርች ቁጭ ብሎ ትምህርት መስማት ብዙም የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም። እግዚአብሔር ስሙ ይባረክ አሁን ላይ በቀን ሁለት ወይንም ሶስት ትምህርቶችን ስሰማ ልውል እችላለሁ። የእግዚአብሔር ቃል ልክ እንደ ምግብ ረሀቤ ሆነ። የምረካው በዚያ ብቻ ሆነ። በዚህ ምስክርነት ውስጥ የእኔን ማንበብ አለመፈለግ እና ድካም የምናገረው፥ እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ የምንለምነውን ሁሉ የሚሰማ፣ እንደ እኔ አይነቷን ሰው ደግሞ የቃሉ ወዳጅ ማድረግ የሚችል አምላክ መሆኑን ሕይወቴ መመስከር ስላለበት ነው።
2ኛ ጸሎት፡- መቼም የጸሎትን አስፈላጊነት እናጣዋለን ብዬ አላስብም። ከአንድ ሰው ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለማሳደግ፥ ከዚያ ሰው ጋር ለማሳለፍ ለማወራት እና ለመጫወት የምትወስዱት ጊዜ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። አብራችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ነው ያንን ሰው ከትላንትና በተሻለ እንድታውቁት፣ እንድትወዱት እና እንድትረዱት ሊያድርጋችሁ የሚችለው። ከአንድ ሰው ጋር ተገናኝታችሁ ቁጭ ብላችሁ ስታወሩ፥ ያንን ሰው “ጊዜዬ ይገባሀል” እያላችሁት ነው እንጂ ሌሎች ልታደርጉ የምትችሉት ብዙ ነገር ይኖራል። ልክ ለስራችን፣ ለጓደኞቻችን እና በሕይወታችን አስፈላጊ ናቸው ብለን ለምናስባቸው ጉዳዮቻችን ጊዜ እንደምንሰጣቸው ሁሉ፥ እግዚአብሔር በጣም እንደምንፈልገው የሚረዳው፥ “እፈልግሀለሁ” የሚለውን ዝማሬ ስንዘምር አይደለም። እንደምንፈልገው ጊዜ እና ትኩረት እየሰጠን በድርጊት ስናሳየው ነው። ታዲያ በዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ ለማሳለፍ በምንሰጠው ጊዜ ውስጥ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ህብረት በማድረግ የውስጥ ሰውነታችን እንዲጠነክር እና በመንፈስ እንድናድግ ትልቅ እድል ይሰጠናል። የእግዚአብሔርን መንፈስ በመለማመድ እናድጋለን፥ ድምጹን በመስማት እናድጋለን፥ ከእርሱ ጋር ህብረት በማድረግ እናድጋለን፥ ነፍሳችንን በፊቱ በማፍሰስ፣ እውነተኛ ልባችንን ለእርሱ በማሳየት ከእርሱ ምክርን ለመቀበል፣ ለመገሰጽ እንዲሁም ፈቃዱን ለመከተል ትክክለኛ ምሪትን በማግኘት እና ሀሳቡን በዘመናችን በመፈጸም እናድጋለን።
3ኛ ህብረት፡- ህብረት መቼም ትልቅ የሆነ የእግዚአብሔር ሀሳብ ነው። ገና ከፍጥረት መጀመሪያ እራሱ እኮ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ብሎ ለአዳም ሄዋንን ሲፈጥርለት በዚህ ህብረት ውስጥ አዳም እርዳታን ያገኝ ዘንድ ነው። እግዚአብሔር ህብረትን የሚወድ የህብረት አምላክ ስለሆነ ነው። ህብረት እያልን ስናወራ ታዲያ ስለ ሰዎች ስብስብ ብቻ እያወራን እንዳልሆነ ማስተዋል መልካም ነው። በምድራችን ላይ ብዙ የህብረት ስብሰባዎች አሉ። አሁን እየተነጋገርን ያለነው ህብረቶች ግን መንፈሳዊ የሆኑ፣ አላማ ያላቸው፣ እድገትን የምናገኝባቸው ህብረቶች ነው። አንዳንዴ በድካም ውስጥ ስንሆን እና ወደ ጸሎት ህብረቶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ህብረቶች እንዲሁም ወደምናገለግልባቸው ህብረቶች ስንሄድ፥ ህብረቱ ውስጥ ከሚሰራው የመንፈስ ቅዱስ ሀይል እንካፈላለን። ወደ ህብረቱ በሄድንበት ድካም እና ዝለት አንመለስም። ሀይልን እንሞላለን፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንሞላለን፣ ጸሎትን እንሞላለን፣ ከነበርንበት ድካም የምንወጣበትን ሀይል እናገኛለን። ውስጣችን ያለውን የጸጋ ስጦታ ደግሞ ለማካፈል ስፍራን እናገኛለን። ብንደክም እንበረታለን፣ ብንስት እንመከራለን፣ ከሌሎች ጋር እጅ ለእጅ መያያዛችን በጀመርነው የመዳን መንገድ ውስጥ ላለን እድገት ትልቅ አስተዋጾ አለው።
ታዲያ በምን በምን እንደግ ካልን፥ በእምነት፣ በየዋህነት፣ በገርነት እና በቸርነት የመንፈስ ፍሬዎችን ሁሉ በማፍራት እግዚአብሔርን በመምሰል ልናድግ ይገባል። ወደ የዋህነት እና ወደ ገርነት ማደጋችንን ትተን፥ ወደ ብልጥነት እና ራስ ወዳድነት እያደግን ያለነው የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ስለማንመገብ ነው። በህይወታችን ጉዳዮች ሁሉ ላይ እግዚአብሔርን ወደ ማመን ማደጋችንን ትተን፥ ወደ ጥርጣሬ እና ወደ አለማመን እያደግን ያለነው፥ ከእግዚአብሔር ቃል መስማት ትተን ከአለም እና ከሰዎች እየሰማን ስለሆነ ነው። ሰው በመንፈሳዊ ህይወቱ እያደገ ሲመጣ እግዚአብሔርን ለማመን የፈጠነ፥ የዋህ፣ ገር፣ ይቅር ባይ፣ ቸርነትን የሚያደርግ፣ ሰዎችን ሁሉ የሚወድ፥ በዚህ አለም አስተያየት ጅል እየመሰለ በእግዚአብሔር አይን ደግሞ ጠቢብ እየሆነ ይመጣል። በነገራችን ላይ ይህቺ አለም የምታስተምረው እንዴት ብልጥ ሆነን፥ ራሳችንን በመውደድ እና በመጥቀም እንዴት የምንፈልጋቸውን ነገሮች እጃችን ማስገባት እንዳለብን እንዴት የተሻለ እና ምቾት ያለው ህይወት መኖር እንዳለብን ነው። የእግዚአብሔር ጥበብ ደግሞ ሲጀምር መጀምሪያው እራሱ እግዚአብሔር አምላካችንን ከመፍራት ነው። ለራስ ከመኖር ይልቅ ለሌሎች መኖርን፣ አካባቢያችን ያሉትን ሰዎች ልክ እንደ ራሳችን መውደድን፣ ልክ እንደ እነ አብርሀም እግዚአብሔርን ቶሎ የሚያምን ገር የሆነ ልብ መኖርን፣ ቶሎ በደልን የሚረሳ የዋህ ልብን፣ ለክርስቶስ ደግሞ ምቾቶቻችንን ሁሉ ጥለን ዋጋ በመክፈል የተጠራንበትን ህይወት መኖርን ነው የእግዚአብሔር ጥበብ የሚያስተምረን። የተጠራነውም ወደዚህ የእግዚአብሔር ወደ ሆነው ጥበብ ለማደግ ነው።
"Our true success in this life is being able to fulfill the purpose we were created for!"