አምልኮ

አንድ በጣም የምወዳት ዘማሪ አንድ ጊዜ አንድ ነገር ስትናገር ሰማሁ እና እውነት ነው አልኩ። ምንድነው ያለችው፥ በህብረት አምልኮቻችን ውስጥ የምናደርጋቸው ስርአቶች በሙሉ እኛን የሚጠቅሙን ናቸው። ለምሳሌ ጸሎቱ ለእኛ ነው፣ ቃሉ ለእኛ ነው፣ ምስክርነቱ ለእኛ ነው፣ ማስታወቂያው ለእኛ ነው፥ አምልኮ ብቻ ግን ለእግዚአብሔር ነው። ከምናደርጋቸው ስርአቶች ውስጥ ለእግዚአብሔር የምንሰጥበት፥ እግዚአብሔር ከእኛ የሚቀበልበት ስርአታችን አምልኯአችን ብቻ ነው። ሆኖም ግን ለዚህ ለእግዚአብሔር ለምንሰጥበት እና ክቡር ለሆነው የእግዚአብሔር ስርአት፥ የሚገባውን ቦታ አንሰጠውም። አምልኮ ብዙ ጊዜ፥ ወይ ወደሚቀጥለው ፕሮግራም መሸጋገሪያ፥ ወይ ደግሞ ሰው ወደ ጉባኤው እስኪገባና እስኪሰበሰብ መቆያ ነገር፥ ልማድ ስለሆነ እንዲያው ካላደረግነው ቅር ቅር የሚለን፥ ብዙ ጊዜ ደግሞ በስሜቶች ብቻ የሚነዳ፥ መንፈሳችን ጋር ሳይደርስ ስጋችንን ብቻ የሚያረካ እና በቃ ከምናረጋቸው ስርአቶች ውስጥ አንዱ ሆኖብናል።  የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ ግን፥ አምልኮ ፍጹም የእግዚአብሔር ሀይል የተገለጠበት፥ አባቶቻችን መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር የተገናኙበት እና ህብረት ያረጉበት፥ የእግዚአብሔር ሀይል እና ስልጣን እንዲሁም ችሎታ የተገለጠበት አስደናቂ ነገር ነው። በነ ኤልሳእ ዘመን በገና ደርዳሪው ልክ በገናውን ሲደረድር የእግዚአብሔር እጅ እንደመጣች እና እግዚአብሔር ለእነዚያ ለሶስቱ ነገስታት ደመናም ዝናብም ሳይኖር ባዶ ሸለቆ በውሀ ሲሞላ ያዩበት መንገድ ሆኗል። አምልኮ በእነ ንጉስ ኢዮሳፍጥ ዘመን ደግሞ ምህረቱ ለዘላለም ነው እያሉ በዝማሬ እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፥ ልክ ምስጋናውን እና ዝማሬውን በጀመሩ ጊዜ ድብቅ የሆነውን ጦር እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ አምጥቶ፥ ድልን በድል ላይ እየጨመረ ባለ ብዙ ድል አርጓቸዋል። እነ ጳውሎስ እና ሲላስን ስንመለከት ደግሞ፥ በመንፈቀ ሌሊት እግዚአብሔርን በዜማ ሲያመሰግኑ እና ሲያመልኩ፥ የብረት ሰንሰለት ከእጃቸው ተበጥሶ፥ የነበሩበት ወህኒ ከነ መሰረቱ ተናውጧል። እውነተኛ አምልኮ ሰንሰለቶች የሚበጠሱበት አስደናቂ ነገር ነው። እኛ ከአምላካችን ጋር በመንፈስ የሆነውን ህብረት የምናረግበት፥ እግዚአብሔር ደግሞ ሲሰራ የምናይበት ነው። እግዚአብሔርን በትክክል ስናመልከው፥ ልክ እንደ ጳውሎስ እና ሲላስ መንፈሳዊ የሆኑ ስውር እስራቶች እና ሰንሰለቶች መበጣጠስ ይጀምራሉ፥ ቀንበሮች መሰበር ይጀምራሉ። የተለያዩ መልሶችን ከእግዚአብሔር እንቀበላለን፥ ልዩ ልዩ መገለጦች ጋር እንደርሳለን። መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ የሆነውን ህብረት ማድረግ እንጀምራለን። 

እነዚህን በአምልኮ ውስጥ ያሉትን በረከቶች ተካፋይ የምንሆነው ግን፥ እግዚአብሔር “አምልኮን እቀበላለሁ” ባለበት በራሱ ባስቀመጠልን መንገድ ስናመልከው ብቻ ነው። በህብረቶቻችን ውስጥ ባሉት የዝማሬ ጊዜያቶች ውስጥ፥ ሁለት አይነት የአምልኮ አይነቶች አሉ። አንደኛው በስጋ የሆነ አምልኮ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንፈስ የሆነ አምልኮ ነው። ሰው በመንፈስ ሳይሆን ሊዘምር ይችላል። ሰው በመንፈስ ሳይሆን ሊያጨበጭብ ይችላል፣ እልል ሊል ይችላል፣ ሊዘል ይችላል፣ ሊጮህ ይችላል፥ ብዙ ነገሮችን ሊያደርግ እና ሊሆን ይችላል። ያ ግን እውነተኛ አምልኮ አይደለም። እውነተኛ የሆነ እና ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮ፥ በሁለት ነገሮች ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባው የእግዚአብሔር ቃል በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 4፡24 ላይ በግልጽ ይናገራል። ቃሉ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስ እና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ይላል። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ ስለዚህ የሚሰገድለት በመንፈስ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ ስለዚህ የምንሰዋለትን መስዋእት የሚቀበለው በመንፈስ ሆነን ስንሰዋለት ነው። በስጋ የሆነ አምልኮ እና በመንፈስ የሆነ አምልኮ በጣም የተለያየ ነው። በስጋ የሆነ ስግደት እና በመንፈስ የሆነ ስግደት በጣም የተለያየ ነው። ሰው በመንፈስ ሳይሆን በስጋው ሊሰግድ ይችላል። በመንፈስ የሆነ ስግደት ግን የስጋ ጉልበታችንን ብቻ ሳይሆን፥ መንፈሳችንን እና ነፍሳችንን እንዲሁም መላው ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር አምላክነት እያስገዛን ሁለንተናችንን በፊቱ የምናዋርድበት ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ፥ የሚቀበለው በመንፈስ የሆነን አምልኮ እና መስዋእት ነው። ስለዚህ ሁልጊዜም ቢሆን በቤተክርስቲያን፣ በህብረት እንዲሁም በግል አምልኮቻችን ውስጥ ለማምለክ ስንዘጋጅ፥ በመንፈስ ለመሆን መዘጋጀታችን በጣም አስፈላጊ ነው። 

በመንፈስ የሆነ አምልኮ ተቃራኒው በስጋ የሆነው አምልኮ ነው። በመንፈስ የሆነው አምልኮ ጠላት በስጋ የሆነው አምልኮ ነው። ይሄ ስጋችን፥ በመንፈስ ለእግዚአብሔር የምናቀርበውን አምልኮ አይደግፈውም። ስጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በስጋ ላይ የሚቀዋወሙ እንደመሆናቸው መጠን፥ ይሄ ስጋችን በመንፈስ የሆነውን አምልኮአችንን የሚቃወም ነው። ስለዚህ የመንፈስ አምልኮ ጠላት፥ የስጋ አምልኮ ነው። የስጋ አምልኮ ፍጹም በመንፈስ ያልሆነ እና በስሜት ብቻ የሚመራ፥ ወይ በሙዚቃው ድምጽ እና በሰው ጩሐት ብዛት እየተጋጋለ፥ ከመንፈስ አምልኮ የሚያወጣ አምልኮ የመሰለ ግን አምልኮ ያልሆነ፥ መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ጋር የማይደርስ እና የእግዚአብሔር ቃል አምልኮ ብሎ የማያውቀው ነገር ነው። ከእውነተኛው አምልኮ ትኩረትን የሚስብ እና አይምⶂችንን በመሰብሰብ በመንፈስ ሆነን እውነተኛውን የመንፈስ አምልኮ በአምላካችን ፊት እንዳናቀርብ ተቃዋሚ ነው። ለዚህ ነው ሰው አጨበጨበ ወይንም ጉባኤው በጩሐት ተሞላ ማለት፥ እግዚአብሔር ተመለከ ብለን መደምደም የማንችለው። በአምልኮ ውስጥ አንጮህም፥ አናጨበጭብም እያልን አይደለም። ግባችን እና አላማችን ግን በመንፈስ በሆነው መገለጥ እና መደነቅ ውስጥ ወዳለው ጩሀት እና ጭብጨባ ጋር መድረስ ነው። አላማችን እግዚአብሔር እቀበለዋለሁ ወዳለው የአምልኮ ስርአት ውስጥ ገብተን፥ አምልኯአችንን ከስጋ ወደ መንፈስ አምልኮ ከፍ በማድረግ፥ መንፈስ ወደ ሆነው አምላካችን ጋር እንዲደርስልን ማድረግ ነው። 

በመዝሙረ ዳዊት 51፡17 ላይ ሲናገር፥ “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” በማለት እንደሚናገረው፥ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መስዋእታችን፥ የተሰበረው መንፈሳችን፥ በፊቱ የምናዋርደው ልባችን እና በገዛ ፍቃዳችን ለእርሱ አምላክነት የምናስገዛው ማንነታችን ነው። መስዋእቱ እኛው እራሳችን ነን። በሮሜ መጽሐፍ ምእራፍ 12 ላይም እንደሚናገረው፥ ሕያው እና ቅዱስ መስዋእት አርገን በእግዚአብሔር ፊት የምናቀርበው፥ ሰውነታችንን እራሳችንን ነው። መስዋእቱ የመድረኩ መብራት እና ጭስ አይደለም። ጭስ የብሉይ ኪዳን መስዋእት ነው፥ የአዲስ ኪዳን መስዋእት አይደለም። እሱም ደግሞ አርቲፊሻል ጭስ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የመረጠው ጣፋጭ የሆነ የእጣን እና የመስዋእት ሽታ ነው። አሁን ግን መስዋእቱ ጭስ አይደለም። መስዋእቱ ግርግሩ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ መስዋእት ያልሆኑት ነገሮች፥ ትኩረታችንን በመውሰድ እውነተኛ የሆነውን መስዋእት በእግዚአብሔር ፊት እንዳናቀርብ እንዳያረጉን ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። እውነተኛ እና እግዚአብሔር የሚቀበለው አምልኮ በመንፈስ እና በእውነት ሆነን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ማንነታችን ነው። የተሰበረው መንፈሳችን፥ የተዋረደው ልባችን እንዲሁም በገዛ ፈቃዳችን ለእርሱ አምላክነት እና ፈቃድ የምናስገዛው መላው ሁለንተናችን ነው። የመንፈስ አምልኮ ጠላት እና ተቃዋሚ ደግሞ በስጋ ሆነን የምናደርጋቸው አምልኮ የመሰሉ ግን አምልኮ ያልሆኑት ነገሮች ናቸው። 

እግዚአብሔርን ለማምለክ የተጠራነው በመንፈስና በእውነት ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ ግን አምልኮቻችን እውነትን የሚለቁበት እና ውሸትን የሚይዙበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ መዝሙሩ “እግዚአብሔር ሆይ ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብዬ አንተን ሳስብህ አድራለሁ” የሚል ዝማሬ ቢሆን፥ ይሄ ዝማሬ በእኛ የግል ህይወት ውስጥ እውነተኛ ነው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ካልሆነ ዝም ማለቱ ይሻላል እንጂ እግዚአብሔር ውሸትን፥ ያልሆነውን ነገር፥ የማናደርገውን ነገር እውነት ነው አምልኮ ነው ብሎ አይቀበለውም። አምልኮ በእውነት እና በመንፈስ ነው። እኛ ግን ብዙ ጊዜ በዝማሬ እግዚአብሔርን ስናመልክ፥ የምናመልከው እውነት ባልሆነ ወይንም በውሸት እና በስጋ ነው። 

እንዴት ነው በመንፈስ ወደ ሆነው አምልኮ የምንገባው? ብለን ከጠየቅን፥ በተለይ በጉባኤው ውስጥ ሆነን በዝማሬ ስናመልክ፥ የአይንን መጨፈንን ጥቅም እንደዚህ የህይወቴ ምእራፍ የተረዳሁት ጊዜ የለም። በተለይ አሁን ባለንበት በዚህ ዘመን፥ መድረክ ላይ የምናያቸው አንዳንድ ነገሮች፥ በመንፈስ ወደሆነው አምልኮ የሚጋብዙ ሳይሆኑ፥ በስጋ ወደሆነው አምልኮ ወደመጋበዝ የሚያደሉ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው። ለምሳሌ ሰው መድረክ ላይ የሚሽከረከር ልዩ ልዩ ቀለም ያለው መብራት እና ጭስ እያየ እንዴት ነው ሀሳቡን መሰብሰብ እና እግዚአብሔርን ማሰብ እራሱ የሚችለው? እንዴት ነው በመንፈስ መሆን የሚችለው? አይን መጨፈን በተለያዩ ነገሮች ሀሳባችን ሳይወሰድ እና ሳይከፋፈል፥ ልናመልክ የቆምነውን እግዚአብሔርን ማሰብ እንድንችል ይረዳናል። በመንፈስ የምንሆነው፥  ሀሳባችንን በመሰብሰብ እና የምንዘምረውን መዝሙር እያስተዋልን በመዘመር ነው። 

መዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 47፡7 ላይ ሲናገር “እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉስ ነውና፥ በማስተዋል ዘምሩ” ይላል። የምንዘምረውን መዝሙር አምልኮ አርገን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው፥ መዝሙሩን የምናውቀው እና ብዙ ጊዜ የዘመርነው ቢሆንም እንኳን፥ እያሰብን እና እያስተዋልን በመዘመር ነው። ለምሳሌ አንድ የመዝሙር ምሳሌ ብንወስድ፥ 

“በምህረት የተሞላህ ታላቅ አምላክ ነህና፥ 

አሁንም አበዛለሁ ከነፍሴ ምስጋና

ኦ በምስጋና በዝማሬ እገባለሁ፥ 

ወደ ማደሪያህ እገባለሁ” 

እያልን ከሆነ የምንዘምረው፡ አይኖቻችንን ጨፍነን የዝማሬውን ትርጉም በደምብ እያስተዋልን ልንዘምር ይገባል። እግዚአብሔር እንዴት በምህረት የተሞላ አምላክ እንደሆነ፥ በህይወታችን ላይ ያደረገውን የምህረት ብዛት እያሰብን፥ በምህረት የተፈራ ታላቅ አምላክ እንደሆነ እያሰብን እና በዚህ ምህረቱ እየተደነቅን እንዲሁም የዝማሬውን እውነተኛነት በነፍሳችን እያጸደቅን አሁንም አበዛለሁኝ ከነፍሴ ምስጋና እያልን፥ የልባችንን ምስጋና ከልባችን ሆነን ከዙፋኑ ስር እናስቀምጣለን። “ኦ በምስጋና በዝማሬ እገባለሁ፥ ኦ ወደ ማደሪያህ እገባለሁ” እያልን ስንዘምር፥ የእግዚአብሔርን ምስጋና እያሰብን፥ ድሮ በብሉይ ኪዳን ዘው ተብሎ ወደ እግዚአብሔር መቅደስ ሊገባ እንደማይቻል፥ ዛሬ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ገብተን ለመሰዋት የተሰጠንን አስደናቂ እድል እያሰብን እንዲሁም በዝማሬው ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እራሱ ወደ ሀሳባችን በሚያመጣቸው ነገሮች እየተደነቅን፥ በመንፈስ ወደሆነው አምልኮ ውስጥ እንገባለን። መዝሙሩ እውነት መሆኑን በልባችን እያረጋገጥን እያንዳንዱን በዝማሬው ውስጥ ያለውን ቃል እያስተዋልን እና ከዝማሬው ጋር እየተስማማን ስንዘምር፥ የእኛ መንፈስ ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር ህብረት እያረገ እራሳችንን እየለቀቅን ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ውስጥ እያሆንን ወደ መንፈስ አምልኮ ውስጥ እንገባለን። እዚህ ውስጥ ነው እንግዲህ እውነተኛ የሆነ ህብረት ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው። እዚህ ውስጥ ነው መልስ ያለው፥ መገለጥ ያለው፥ የእግዚአብሔር ድምጽ ያለው፥ የአይን መከፈት ያለው፥ ምሪት ያለው፥ ፈውስ ድንቅና ተአምራት ያለው። እግዚአብሔር መንፈስ ነውና፥ የሚመለከው እና የሚሰገድለት በመንፈስ ብቻ ነው።

"Our true success in this life is being able to fulfill the purpose we were created for!"

for the Kingdom through Christ !

©2026, Hana Elias. All Rights Reserved

Scroll to Top